AMN ኅዳር 25/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአገራችን የመጀመሪያ በሆነ የግንባታ ቴክሎጂ በላፍቶ ሳይት 26 ሺህ ቤቶችን ስራ ማስጀመራቸውን ገለጹ፡፡
በዚህ ዓመት ከተያዘው ዋነኛ እቅዶች መካከል ቀዳሚው ለከተማው ነዋሪዎች የቤት አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የከተማ አስረዳደሩ በዚህ ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ እቅዱን በጥራትና በፍጥነትን እውን ለማድረግ ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን Cold-Formed Steel (CFS) የግንባታ ቴክኖሎጂን መጠቀም አንድ አማራጭ ተደርጎ ዛሬ ስራ አስጀምረናል ብለዋል።

ይህ ቴክኖሎጂ በሌላው ዓለም የተለመደ ሲሆን፣ ቤቶችንም ሆነ ህንፃዎችን በፋብሪካ ውስጥ የሚገጣጠሙ ብረቶችን በመጠቀም ወለልን፣ ግድግዳና ጣሪያን ጨምሮ ሁሉንም ክፍል በፍጥነትና በጥራት ማምረት የሚያስችል አሰራር ነው።
የዚህን የቴክኖሎጂ ፋብሪካ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የተተከለ ሲሆን፣ በፈጠራና ፍጥነት መርህ ግንባታን ከሳይት ወደ ፋብሪካ በመቀየር የግንባታ ፍጥነትን በማሳደግ፣ ወጪን በመቀነስና ጥራትን በማሻሻል አንጻር ተመራጭ ነው።
አስተዳደራችን እንደወትሮው የነዋሪውን ጥያቄ ለመመለስ እና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በጠንካራ የፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ዲስፕሊን እና በ24/7 የስራ መርሃ ግብር ፕሮጀክቱ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቅቆ ለታለመለት አላማ እንዲውል ይደርጋል።
ይህን ከከተማችን አልፎ ለአገር ጠቃሚ የሆነ ቴክኖሎጂን ወደ አገር ይዘዉ የመጡትን የሌጋሲ ሆም ድርጅት ባለቤት ኢንጂነር ያሬድ አፈወርቅን በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመሰግናለሁ ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል ።