ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ አጸደቀ

You are currently viewing ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ አጸደቀ

AMN ህዳር 25/2018

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ አጽድቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።

ከጸደቁ ረቂቅ አዋጆች መካከል የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ይገኝበታል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር በማያያዝ ያነሱት የነበረውን ቅሬታ በመፍታት ለሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂ እና ንፁህ የኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገው የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አጽደቋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም አጽድቋል።

በኢትዮጵያና ቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት እንዲሁም ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያና በብራዚል መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና በኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review