ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተደረገው ዘላቂ ሰላም ስምምነት ለክልሉ ሕዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገለጹ

You are currently viewing ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተደረገው ዘላቂ ሰላም ስምምነት ለክልሉ ሕዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገለጹ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ህዳር 25/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ለሰላም መቼም ቢሆን ረፍዶ አያውቅም በማለት ባሰፈሩት መልእክት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረገው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ለክልሉ ሕዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ዜጎችን ከሞት አደጋ ወደ ሕይወት የመለሰና አዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱና ተስፋቸው እንዲለመልም ያደረገ ነው፡፡ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያውያን በመነጋገር ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ በድጋሚ አሳይቷል፡፡

አጉል ጀብደኝነት ወደ ግጭት ያመራል፤ ጦርነት ደግሞ ውዱን የሰው ሕይወትን ይቀጥፋል፤ በብዙ ጥረት የተገኘን ሀብትንም ያወድማል፤ ብሎም ድህነትን፣ ድንቁርናንና ኋላ ቀርነትን ያስፋፋል። በመሆኑም ጥፋት ከሚያስከትሉ ተግባራት በመራቅ ለዘላቂ ሰላማችንና ለልማታችን በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

መንግሥት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያለውን ጽኑ አቋም አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል። እንደዛሬውም ተግባራዊ ርምጃ ይወስዳል። በመሆኑም ነፍጥ አንሥተው በጫካ የሚገኙ የተወሰኑ ቀሪ ቡድኖች በኃይል የሚሳካ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ወደ ሰላም ሊመጡ ይገባል።

የዛሬውን የሰላም ስምምነት ለማዝለቅ፣ የግጭት ተግባራትን በጋራ በማውገዝ ለሰላም ዘብ መቆም ያሻል፡፡ ይህ ስምምነት እንዲሳካ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ስም ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ ለሕዝብ ሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review