አዲስ አበባ በዘርፈ ብዙ አበርክቶዋ የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማትን እንድታስተናግድ ተመርጣ ኃላፊነቷን በብቃት እየተወጣች ትገኛለች

You are currently viewing አዲስ አበባ በዘርፈ ብዙ አበርክቶዋ የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማትን እንድታስተናግድ ተመርጣ ኃላፊነቷን በብቃት እየተወጣች ትገኛለች
  • Post category:አፍሪካ

AMN ህዳር 25/2018 ዓ.ም

በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ያለችው የአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የፓን-አፍሪካ የሚዲያ ሽልማትን ከትላንት ጀምሮ እያስተናገደች ሲሆን፣ ሥነ-ሥርዓቱ ዛሬ ምሽት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

አዲስ አበባ የ2025 የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማትን (AMA) ለማስተናገድ የተመረጠችው በነበራትና አሁንም ይበልጥ አጠናክራ ባስቀጠለችዉ ፈርጀ ብዙ አበርክቶዋ ሲሆን ከተማዋ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ዋና ከተማ ከመሆኗም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሳየችው ከፍተኛ ለውጥ ምክንያት ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት እና የፓን-አፍሪካኒዝም ማጠንጠኛ በመሆኗ፣ በአፍሪካ የነጻነት አባቶች ልጆች እና በአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ ትብብር የተዘጋጀውን የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ለማስተናገድ ትክክለኛዋ ምርጫ መሆናም ታዉቋል።

አዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሠራችው ሥራ ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የሚወዳደር ለውጥ እያመጣች በመሆኗ በዚህ ምክንያትም በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤዎችን ጨምሮ የተለያዩ አፍሪካን የተመለከቱ መድረኮች፤ የመላው አፍሪካ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ሥራ አስፈፃሚዎች እና የፖለቲካ መሪዎች በደንብ የሚያውቋት መሰብሰቢያቸው ጭምር መሆን በመቻሏ ለዛሬዉ ታሪካዊ መድረክ ለማስተናገድ በቅታለች።

በሌላ በኩልም ከመላው አህጉሪቱ እና ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎችን በምቾት የሚያተናግደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መገኛ አዲስ አበባ መሆኗ የሽልማቱ እጩዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲመርጧት ያስቻላት መሆኑም ታዉቋል።

ሽልማቱ ትክክለኛ የአፍሪካ ፍላጎት መገለጫ እንዲሆን የታሰበ ሲሆን፣ አዘጋጆቹ ይህን መስፈርት የምታሟላ እና የፓን አፍሪካ መነሻ የሆነችው አዲስ አበባ እንደሆነች በመተማመን ዝግጅቱ በአዲስ አባባ እንዲካሄድ ያደረጉ እዉነታዎች ናቸዉ ተብሏል።

በውድድሩ ከ40 ሀገራት የተውጣጡ ከ800 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የአፍሪካ ነፃት አባቶች ልጆች እና የዋና ዋና መገናኛ ብዙኃን ሥራ አስፈፃሚዎች የዝግጅቱ ታዳሚዎች ናቸው።

የአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ፣ የፓትሪስ ሉሙምባ ፋውንዴሽን፣ የክዋሜ ንክሩማህ ፋውንዴሽን፣ የምዋሊሙ ኒዬሬሬ ፋውንዴሽን፣ የኬኔት ካውንዳ ሌጋሲ ፋውንዴሽን፣ የሲሱሉ ፋውንዴሽን ለማኅበራዊ ፍትህ እና የፒኤልኦ ሉሙምባ ፋውንዴሽን ከዝግጅቱ ዋና አጋሮች መካከል እንደሆኑም ተረጋግጧል።

ከ800 ተወዳዳሪዎች መካከል ሃያ አንዱ እጩዎች በተለያዩ ምድቦች ዛሬ ምሽት አሸናፊውን ይፋ ለሚያደርገው ፍጻሜ የደረሱ ሲሆን የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት በጋዜጠኝነት፣ በብሮድካስቲንግ፣ በዲጂታል ሚዲያ እና በትርክት ግንባታ የአፍሪካ ስኬቶችን ያሳዩ የሚዲያ ተወካዮች በአንድነት የሚሳተፉበት እና የሚሸለሙበት ተብሏል።

የሽልማት ዝግጅቱ አፍሪካውያን ስለማንነታቸው እና የአፍሪካ ሕዝቦችን ደማቅ ማንነት በራሳቸው እንዲተርኩ የሚያስችላቸውን ዕድል እንደሚከፍትላቸው የሁነቱ አጋር የሆነው አር.ቲ መዘገቡ ታዉቋል። -የኢዲስ አበባ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review