የአጥንት ቲቢ በሽታ ምንድነዉ?

You are currently viewing የአጥንት ቲቢ በሽታ ምንድነዉ?
  • Post category:ጤና

AMN ህዳር 26/2018

ቲቢ በሽታ በዋነኝነት የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ግን ማንኛውንም የሰውነት አካል ማጥቃት የሚችል በባክቴርያ የሚመጣ እና በትንፋሽ የሚተላላፍ በሽታ ነው፡፡

ከሳንባ ሽፋን ጀምሮ፣ ጉሮሮን፣ ልብን፣ ኩላሊትን፣ አንጀትን የአጥት ክፍሎችን ሊያጠቃ የሚችል ህመም መሆኑን በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቲቢ እና ተያያዥ በሽታዎች ሀኪም እና ተመራማሪ ዶ/ር ሚሊዮን ሞላ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ሲቪየር ፎሮም ኦፍ ቲቢ እና ነን ሲቪየር ፎርም ቲቢ የሚባሉ ሁለት አይነት የቲቢ በሽታ አይነቶች መኖራቸዉን የሚገልጹት ዶ/ር ሚሊዮን ሞላ ሲቪየር ፎርም ተብሎ የሚጠራው የአጥንት ክፍልን የሚያጠቃ የቲቢ አይነት፤ በአብዛኛው የጀርባ አጥት አከርካሪን የሚያጠቃ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2023 ከ ቲቢ ጋር በተያያዘ ባወጣው ሪፖርት ከቲቢ ጋር ከተያያዙ ህመሞች መካከል ከአንድ እስከ አምስት በመቶ የሚሆነው የአጥንት ቲቢ ሲሆን ከ70 ከመቶ በላይ የሚሆነው ደግሞ በአብዛኛው አከርካሪን የሚያጠቃው መሆኑን አስፍሯል፡፡

ከሳንባ ውጭ የሆኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ የቲቢ በሽታ ሲከሰት በቀላሉ ምልክት ማግኘት ሊያስቸግር ይችላል ብለዋል።

የአጥንት ቲቢ ከሌሎች ህመሞች ለየት የሚያደርገው በህመም ማስታገሻዎች የማይጠፋ መሆኑ እና በሂደት አጥንት ወደ መስበር ደረጃ መድረሱና ብሎም ለረጅም ጊዜ የማይጠፋ ህመም መኖሩ ነው።

ከረጅም ጊዜአት በፊት ቤተሰብ ውስጥ የታመመ ሰው ካለ፤ በስራ ቦታ ላይ ቲቢ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ከነበረ ሊተላለፍ እና እስከ ሀያ አምስት ዓመት ሳይታወቅ ሊቆይ ይችላል ብለዋል።

ለመራመድ መቸገር መገጣጠምያ ላይ ኩምትር የማለት፤ የአጥንት ቲቢ ምልክቶቹ ናቸው ሆኖም እንደነ ሪህ እና ከሌሎች የመገጣጠሚያ ህመሞች ጋር የመመሳሰል በህሪ ስላለው ቶሎ ላይታወቅ ይችላል ሲሉ ዶ/ር ሚሊዮን ሞላ ያብራራሉ፡፡

መደረግ ካለበት ጥንቃቄ ጋር በተያያዘም አንድ የቲቢ ህመም ያለበት ሰው ሲያስነጥስ ሌሎች ሰዎችን ሊያስያዝ ስለሚችል መስኮት እና በር በመክፈት አየር በደንብ እንዲገባ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አንድ ማሳል የጀመረ የቲቢ ታማሚ ለሶስት ወር ያህል በሽታን ሊያስተላልፍ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

ከህክምና ጋር ተያይዞም አጥንት ጠንካራ ስለሆነ አጥትን አልፎ የሚሄድ መድሃኒት ከተሰጠ ለአንድ አመት ያህል ታክሞ መዳን ይቻላል ሲሉ መክረዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review