ጠንካራ ፌደራላዊ ሥርዓት ለመገንባት የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማክበር እና ማስከበር እንዲሁም ለሃገራዊ አንድነትና ጥቅም በጋራ መቆም ያስፈልጋል ሲሉ የፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አመራር እና አስተዳደር ኮሌጅ ምክትል ዲን መሀመድ አሊ (ዶ/ር) ገለጹ።
መሀመድ አሊ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የፌዴራሊዝም ስርአቱ ብዝሃነት ከማስተናገድ ባሻገር የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፖለቲካ ተሳትፎ ጠንካራ እና ቀጥተኛ እንዲሆን ማስቻሉን አንስተዋል፡፡
በንጉሳዊውም ሆነ በደርግ ስርዓት ውስጥ የብሔር ብሄረሰቦች ጥያቄ በአግባቡ አለመመለሱን የገለጹት መሀመድ አሊ (ዶ/ር)፣ የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የፌዴራል ስርአት እንዲጀመር እና ክልሎች እንዲመሰረቱ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢህአዴግም ቢሆን በጣም ጥቂት ፓርቲዎችን ብቻ ወደ ራሱ በመቀላቀል ሌሎቹን ማግለሉን ነዉ የተናገሩት፡፡
የፌዴራል ስርዓቱ ብሔሮች ፤ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የራሳቸውን ቋንቋ ከማሳደግ አንጻር የትምህርት የፖሊሲ እና ማዕቀፋቸውን በማዘጋጀት በራሳቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው የሚያደርግ ቢሆንም፣ በፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ ገብነት የተነሳ እውነተኛ የውሳኔ አካል አልነበሩም ብለዋል።
የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ ግን ብዙ መልካም ለውጦች መታየታቸውን የሚናገሩት መሀመድ አሊ (ዶ/ር)፣ የፌዴራል ስርአቱ ተጠናክሮ ወደፊት እንዲቀጥል ትልቅ መሰረት መጣሉን ጠቁመዋል፡፡

አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ ከመፍጠር እና ህብረብሄራዊ አንድነትን ከማጠናከር አንፃር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አመላክተዋል፡፡
ሃገራዊ ችግሮቻችን ሰፊ በመሆናቸው የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸዉና ወደ መሀል እንዲመጡ ፤ ሀገራቸውን በባለቤትነት እንዲይዙ እና የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ ከለዉጡ ወዲህ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረዉ ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ስርአቱ ጠንካራ እንዲሆን የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማክበር እና ማስከበር እንዲሁም ለሃገራዊ አንድነትና ጥቅም በጋራ መቆም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በፍሬህይወት ብርሃኑ