ሆሳዕናዎች አንግዶቻቸውን ሃባይ ጡምን ዋተኮ – በማለት እየተቀበሉ ነው።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ህዳር 29/2018 ዓ.ም ይከበራል።
ታዲያ በዓሉን ለመታደም በሆሳዕና ከተማ የተገኘው የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚዲያ ቡድን ወደ ሆሳዕና ከተማ የሚወስዱ መንገዶች ላይ የሚገኙ የክልሉ ከተሞች፣ በክልሎች እና በፌዴራል ሰንደቅ ዓላማ ተሸቆጥቁጠውና አምረው “ሃባይ ጡምን ዋተኮ” በማለት በባህላዊ አልባሳት ደምቀው እንግዶቻቸውን ለመቀበል ዳስ ጥለው እየተጠባበቁ መሆቸውን ታዝቧል::
በትላንትናው ዕለት “የወንድማማችነት ቀን” በአካል ብቃት እንቅስቃሴና የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል::
በዛሬው ዕለት ህዳር 26/2018 ዓ.ም ደግሞ “የአብሮነት ቀን” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ የበዓሉ ተሳታፊዎች ወደ ከተማ የሚገቡበት ቀን ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹን ለመቀበል በከተማዋ መግቢያ በሮች ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ባዛር እና ኤግዚብሽን ደግሞ በወልቂጤ ከተማ ህዳር 28/2018 ዓ.ም የሚከፈት ይሆናል::
ይህንን በጉጉት የሚጠበቅ በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር ሆሳዕና ከተማ ከወዲሁ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ የከተማዋ ጎዳናዎችም በሰንደቅ ዓላማዎች ደምቀዋል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ ሌሎች የሃገራችን ከተሞች የተስፋፋው የኮሪደር ልማት ስራም በሆሳዕና ከተማ በመተግበሩ፣ የከተማዋን ገፅታ ውብና ማራኪ አድርጐታል፡፡ 24/7 የስራ ባህልም እየተተገበረ ነው፤ ይህንንም ቡድኑ በምሸት ቅኝቱ ለመታዘብ ችሏል::
በያለው ጌታነህ