AMN- ህዳር 25/2018 ዓ.ም
የአሰላ ከተማ ነዋሪዋ ታዳጊ ዱረቲ አወል እንደ እድሜ እኩዮቿ ቦርቃ ለመጫወትና የምትጓጓለትን ትምህርቷን በጥሩ ውጤት አጠናቃ ለመጨረስ አልታደለችም።
በተፈጥሮ የገጠማት የልብ ቧንቧ ክፍተት እንደ እድሜ እኩዮቿ 11ኛ ክፍል መድረስ ቢኖርባትም 9ኛ ክፍል ላይ እንድታቋርጥ ምክንያት መሆኑን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ገልፃለች።
የልብ ህክምናው ወጪው ከፍተኛ መሆን ብሎም ከሀገር ውጭ መሰጠቱና ይህም ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦቿ የሚቻል አለመሆኑ ሌላኛው የመኖር ተስፋዋን ያቀጨጨ መሆኑ ለከፋ ጭንቀት እንደዳረጋት ታብራራለች።
አባቷ አወል በያንም፣ ህመሟ ከታወቀ በኋላ ለማሳከም ያላቸውን ጥሪት እንኳን ቢያወጡ የህክምና ወጪውን መሸፈን አለመቻሉ ቤተሰቡንም ለከፋ ጭንቀት የዳረገ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በተለይም ልጃቸው በጊዜ ህክምና ካላገኘች ህይወቷ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ከህክምና ባለሙያዎች የተሰጣቸው ምክር ከባዱን የሠው ፊት እንዲያዩም ያደረገ ጉዳይ መሆኑን በትካዜ አብራርተዋል።
አዲስ አበባ የሚገኘው ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ከቻይና የሚመጡ የህክምና ቡድኖች በከፋ የልብ ህመም ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውን ዜጎች ሙሉ የነፃ ህክምና ዕድል እንደሚሰጥ የወጣውን ማስታወቂያ በመመልከት አስፈላጊውን ሰነድ በማሟላት ይመዘገባሉ።
የቤተሰቡ ጭንቀት እየጨመረ በነበረበት አጋጣሚ ያገኙት ይህ እድል፣ ለልጃቸው ያለው ብቸኛ አማራጭ መሆኑን በመረዳት የዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ቀን በጉጉት ሲጠብቁ መቆየታቸውንም ያስረዳሉ።

ባልጠበቁት አጋጣሚ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ሆስፒታሉ ሲያበስራቸውም በደስታ ማንባታቸውንም ያስታውሳሉ።
በሆስፒታሉ አማካኝነት ከቻይና የመጣው በጎ ፍቃደኛ የህክምና ቡድን፣ ልጃቸውን ለተሻለ ህክምና ወደ ቻይና በመውሰድ የልብ ቀዶ ህክምና በማድረግ ፈውስ እንድታገኝ ረድቷታል።
የልጃቸው ጤና መመለሱ ያስደሰታቸው አቶ አወል፣ ሆስፒታሉ አስተማሚን ጨምሮ ሁሉን ነገር በነፃ ላደረገላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
ታዳጊ ዱረቱ በበኩሏ፣ ያቋረጠችውን ትምህርት በመቀጠል ዶ/ር የመሆን ህልሟ እንዲሳካ ላደረጉ የህክምና ቡድኖች ምስጋናዋን ያቀረበች ሲሆን፣ በጎ ማድረግን ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ ተግባር መሆኑን አንስታለች።
በተመሳሳይ ላለፉት 3 ዓመታት በልብ ህመም ስትሰቃይ የቆየችው ህፃን ማሪያማዊት የዕድሉ ተጠቃሚ በመሆን ፈውስን አግኝታለች።
ሳያውቁን ድንበር አቋርጠው በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የልጃችንን ጤንነት የመለሱ ቻይናውያን የሰብአዊነት ልክ ማሳያ ከመሆናቸውም በላይ ሌሎችም ይህንኑ ሊያጠናክሩበት የሚገባ ነው ሲሉ የህፃኗ ቤተሰብ ዘአማኑኤል ደርቤ ተናግረዋል።
እያደገ የመጣው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የበርካቶችን ህይወት በመቀየር የመኖር ተስፋን እያለመለመ በመሆኑ፣ መሰል ተቋማትም በዚህ የተቀደሰ ተግባር በመሳተፍ የበርካቶችን ሸክም ቢያቀሉ መልካም እንደሆነ ገልፀዋል።

ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል በሀገር ውሰጥ የልብ ህክምናን ማድረግ ያልቻሉ 3 ለሚሆኑ ታዳጊዎች እና አስታማሚዎች ከ3.5 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የነፃ ህክምናውን በቻይና እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጿል።
ሆስፒታሉ በየዓመቱ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የነፃ ህክምና እየሰጠ ሲሆን፣ እስካሁንም ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን የሆስፒታሉ የነርስ ዳይሬክተር ሲ/ር እየሩሳሌም አስራት ይናገራሉ።
የሆስፒታሉ ምስረታን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ ለሚከናወነው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እስከ 20 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
ይህ ሰብዓዊ ተግባር ሆስፒታሉ በጤናው ዘርፍ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ከፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ከማሳየት ባሻገር፣ በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጥልቅ ወዳጅነት እና ትብብር አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑንም አመላክተዋል።
በሚካኤል ህሩይ