የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ፣ ኢትዮጵያን በእብሪት ለመውረር በተነሳበት 1969 ዓ.ም፤ የሀገራቸው መደፈር አንገብግቧቸው ታላቅ ተጋድሎ ከፈጸሙ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች መካከል የሀድያ ተወላጅ የሆኑት ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ አንዱ ነበሩ።
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከሻዕቢያ ጋር በገባበት ጦርነትም እስከ 1977 ዓ.ም ድረስ ታላላቅ ጀብዱዎችን ፈጽመዋል።
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም፤ የሀገራቸው ሉዓላዊነት አንገብግቧቸው ተዋጊ ጄታቸውን ይዘው ተሰልፈዋል።
ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ ላበረከቱት አስተዋጽኦም “የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ” ተሸላሚ ሆነዉ ነበር።
የሆሳዕና ከተማም ለዚህ ውድ ልጇ በ2014 ዓ.ም መታሰቢያ ሐውልት አቁማለች።
ይህ ሃዉልት ለሆሳዕና ከተማ ልዩ መለያዋና ገጽታዋ ሆኗል።
የኢትዮጵያዊው ጀግና ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሐውልት፣ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል እያዘጋጀች ለምትገኘው ሆሳዕና ከተማ ልዩ ገጽታ ሆኗታል።
የፊታችን ህዳር 29 ለሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ለማክበር እንግዶቿን በመቀበል ላይ ለምትገኘው ሆሳዕና ከተማም ልዩ ድባብን አላብሷታል።
ሐውልቱ ከ17 ሜትር በላይ እንደሚረዝምም መረጃዎች ያመላክታሉ።
በበላይሁን ፍስሃ