ከሰላም የሚገኘው ትርፍ እልፍ ነው

You are currently viewing ከሰላም የሚገኘው ትርፍ እልፍ ነው
  • Post category:ፖለቲካ

AMN- ህዳር 26/2018 ዓ/ም

ከሰላም የሚገኘው ትርፍ እልፍና የሁሉንም አካላት አሸናፊነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ሌሎችም የሰላምን መንገድን ሊከተሉ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ትናንት የተፈረመው የሰላም ስምምነትም ለክልሉ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምንና እፎይታን የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ትናንት መፈራረማቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሰላም ስምምነቱ ለህዝቡ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ግጭቶች እንዲቆሙና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የራሱን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

አሁን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተፈረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ሰላምን ማምጣት የሚያስችል እና ሕዝቡም በሰላም ወጥቶ እንዲገባና እንዲሰራ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ጉባኤው በዘላቂ ሰላም ስምምነቱ የተሰማውን ደስታ ገልጸው፤ ስምምነቱ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታትን ጉልህ ፋይዳ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተስተጓጉሎ የቆየው የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በመደበኛነት እንዲሳለጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል፡፡

ከሰላም የሚገኘው ትርፍ እልፍ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ ለሁሉም ሰላምን ቀዳሚ ምርጫ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ለማጽናት መልካም ጅማሮ መሆኑን አንስተው፤ ለስምምነቱ ተፈጻሚነትና ለዘላቂ ሰላም ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሌሎች ቀሪ ኃይሎችም የተፈረመውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ፈለግ ሊከተሉ እንደሚገባ በመግለጽ፤ ምርጫቸው የሰላም መንገድና ሀሳብ ብቻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከግጭት ይልቅ የውይይትና የሀሳብ ልዕልና መር ጉዞ ዘመን ተሻጋሪ ውጤት እንደሚያመጣ ጠቁመው፤ የሰላም መንገድ ሁሉንም አካላት አሸናፊ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረም ላከናወኑት ተግባር አመስግነዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review