AMN – ህዳር 26/2018 ዓ/ም
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ አስረክቧል።
አጀንዳዎቹን የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች አመራሮች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አስረክበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አጀንዳዎችን መረከቡን አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ኮሚሽኑ ሲቋቋም ጀምሮ ሂደቱን እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል።
ፓርቲው የተደራጀ አጀንዳ በማስረከቡ በኮሚሽኑ ስም ያመሰገኑት ዋና ኮሚሽነሩ፤ አጀንዳዎቹ ለሀገራዊ ጉባኤው ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል።
የምክክር ሂደቱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ኮሚሽነሩ ሂደቱ እንዲሳካ የፓርቲዎች ትብብር በቀጣይ ጊዜያትም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገራችንን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢዜማ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማገዝ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
ኢዜማ በሁለት ከተማ አስተዳደሮችና በ11 ክልሎች በተደረጉ የምክክር ምዕራፎች በስፋት መሳተፉን በዚሁ ወቅት መገለጹን ኮሚሽኑ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል።