አዲስ አበባ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ሁነቶችና ኮንፈረንሶችን እንድታዘጋጅ በበርካቶች ዘንድ እንዴት ተመረጠች?

You are currently viewing አዲስ አበባ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ሁነቶችና ኮንፈረንሶችን እንድታዘጋጅ በበርካቶች ዘንድ እንዴት ተመረጠች?

AMN – ህዳር- 26/2018 ዓ. ም

አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት የለውጥ አመታት ተመራጭ ከተማ እንድትሆን የሚያስችሏትን በርካታ ተግባራትን አከናውናለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታ በመቀየርና ዘመናዊና ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን ያስቻላት የኮሪደር ልማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡

ይህም አዲስ አበባ የቱሪዝም የስህበት ከተማ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ሁነቶችና ኮንፈረንሶች የሚካሄዱባት ተመራጭ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

በመዲናዋ የተገነቡ እንደ የአድዋ ድል መታሰቢያ እና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ያሉ ዓለም አቀፋዊ ደረጃቸውን የጠበቁ ተቋማት እንዲሁም ሆቴሎች መገንባታቸው የአዲስ አበባ ከተማ ተመራጭ የኮንፍረስ ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አድርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሰፈነው አስተማማኝ ሰላምና ደህንነትም ከተማዋ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን እንድታስተናግድ ያስቻላት ሌላኛው መስፈርት ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታትም አዲስ አበባ ከተማ ባከናወነቻቸው አስደናቂ ተግባራት ምክንያት በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት አስተናግዳለች፡፡

ስለዚህ መዲናዋ ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን ማስተናገድ መቻሏ በፖለቲካ መሪዎች፣ በመላው አፍሪካ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሥራ አስፈፃሚዎች ዘንድ እውቅና እንድታገኝ አስችሏታል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የፓን-አፍሪካ የሚዲያ ሽልማት መርሀ ግብርን በትናንትናው እለት አስተናግዳለች፡፡

መዲናዋ የ2025 የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማትን (AMA) ለማስተናገድ የተመረጠችው በነበራትና አሁንም ይበልጥ አጠናክራ ባስቀጠለችዉ ፈርጀ ብዙ አበርክቶዋ ሲሆን፣ ከተማዋ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ዋና ከተማ ከመሆኗም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሳየችው ከፍተኛ ለውጥ ጭምር እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት እና የፓን-አፍሪካኒዝም ማዉጠንጠኛ በመሆኗ፣ በአፍሪካ የነጻነት አባቶች ልጆች እና በአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ ትብብር የተዘጋጀውን የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ለማስተናገድ ትክክለኛዋ ምርጫ መሆኗም ታዉቋል።

ሌላው አዲስ አበባ ከተማ የፓን-አፍሪካ የሚዲያ ሽልማትን እንድታዘጋጅ ካስቻሏት ምክንያቶች መካከል፣ ከመላው አህጉሪቱ እና ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎችን በምቾት የሚያተናግደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መገኛ አዲስ አበባ መሆኑ፣ የሽልማቱ እጩዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲመርጧት ያስቻላት መሆኑም ታዉቋል።

በውድድሩ ከ40 ሀገራት የተውጣጡ ከ800 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የአፍሪካ ነፃነት አባቶች ልጆች እና የዋና ዋና መገናኛ ብዙኃን ሥራ አስፈፃሚዎች የዝግጅቱ ታዳሚዎች ሆነዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ፣ የፓትሪስ ሉሙምባ ፋውንዴሽን፣ የክዋሜ ንክሩማህ ፋውንዴሽን፣ የምዋሊሙ ኒዬሬሬ ፋውንዴሽን፣ የኬኔት ካውንዳ ሌጋሲ ፋውንዴሽን፣ የሲሱሉ ፋውንዴሽን ለማኅበራዊ ፍትህ እና የፒኤልኦ ሉሙምባ ፋውንዴሽን ከዝግጅቱ ዋና አጋሮች መካከል ናቸው።

የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት በጋዜጠኝነት፣ በብሮድካስቲንግ፣ በዲጂታል ሚዲያ እና በትርክት ግንባታ የአፍሪካ ስኬቶችን ያሳዩ የሚዲያ ተወካዮች በአንድነት የተሳተፉበት እና የተሸለሙበትም ነው።

የሽልማት ዝግጅቱ አፍሪካውያን ስለማንነታቸው እና የአፍሪካ ሕዝቦችን ደማቅ ማንነት በራሳቸው እንዲተርኩ የሚያስችላቸውን ዕድል እንደሚከፍትላቸው የሁነቱ አጋር የሆነው አር.ቲ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review