AMN ኅዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም
ሦስቱን የፊት ጥርሶቹን አጥቷል ፣ የ2015 የኢትዮጵያ የጁኒየር ሻምፒዮን የሆነ ፣ በአፍሪካ ከ108 ጋላቢዎች 7ኛ ያጠናቀቀ ፣ እንደ ቱር ደፍራንስ ያሉ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ህልም አለው።
በ4 ሺ ብር የኪስ ገንዘብ ከመቀለ – አዲስ አበባ -ከአዲስ አበባ ሞምባሳ በራሱ ወጪ ሀገሩን ያስጠራ የወልዋሎ አዲስ መድሃኒት ፋብሪካ አዲስ ፈራሚው፦ ብስክሌተኛ አማኑኤል ተክለሃይማኖት።
ትውልድ እና እድገቱ አዲግራት ከተማ ነው፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብስክሌት ብሄራዊ ቡድን ስፖርተኛ፡፡ ያኔ በተማሪነት እድሜው ከቤት እስከ ትምህርት ቤት ያለውን የ7 ኪ.ሜ ርቀት ለትራንስፖርት ይጠቀምበት የነበረው ብስክሌት ዛሬ የህይወቱ አንድ አካል ሆኖል።
በአዲግራት ብስክሌት እንደ ባህል ይቆጠራል የሚለው አማኑኤል ተክለሃይማኖት 10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ዓመታዊ የትምህርት ቤቶች የብስክሌት ውድድር ላይ ት/ት ቤቱን /የአለም ብረሃን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትን/ ለመወከል ወደ ወድድር እንደገባ ያስታውሳል፡፡
ትልቅ ህልም መሰነቅ የጀመረው የወቅቱ ብለቴና ከዓመት በኋላ የከተማዋን ወረዳ ወክሎ ተወዳደረ፡፡
በልጁ ብቃት የተማረኩት አሰልጣኞችም “ደስታ የአልኮል ፈብሪካ” የተሰኘ የማውንቴን ቲም ቀላቀሉት፡፡ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ መቀለ የሚገኘው ጉና ከዛም አሁን ላይ የወልዋሎ አዲስ መዳኒት ፋብሪካ ፈራሚ ሆኗል፡፡

ብስሌተኛ አማኤል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት በስፖርቱ ከፍ ያለ ደረጃ እንዳይደርስ ትልቅ እንቅፋት እንደነበር ያስረዳል፡፡ ከአስከፊው ጊዜ በኋላም ተስፋ ሳይቆርጥ የ2015 የኢትዮጵያ የጁኒየር ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ አማኑኤል ህልሙን ለመኖር የተስፋ ጭላጭል በተመለከተበት ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች እውን ለማድረግ እንደተቸገረ ይገልፃል፡፡
በተለይ ኔዘርላንድስ ሃገር ሚገኝን ክለብ/ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያተኮረ/ ለመቀላቀል ቢቃረብም ተጨናግፏል። በደቡብ አፍሪካ የሚሰጥ የካሚፒንግ ስልጠናን /UCI south Africa camping / እድሎችን አግኝቶ ከቪዛ ጋር በተያያዘ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
ከዓመት በፊት አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ዓመታዊ የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ በኢሊት ካታጎሪ ተወዳድሮ ብስክሌተኛው 3ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ስልጠና ብሎም በአፍሪካ ትልቅ ወድድር ላይ የሚያሳትፈውን እድል ያገኘው አማኑኤል ከኮንቲኔታል ፕሮ ኮንቲነታል ክለብ ተወዳዳሪዎች ጋር በመፋለም በኪጋሊ ምድር በመጀመሪያ ውድድሩ 9ኛ ሆኖ አጠናቋ።
ባለፉት ሁለት አመታት የትግራይ ክልል ሻምፒዮን የሆነው የአዲግራቱ ተወላጅ ዘንደሮ በተካሄደው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በራሱ ወጪ በጎረቤት ኬኒያ አዲስ ታሪክ ሰርቶ ተመልሷል፡፡
የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ለብስክሌተኛ የተለየ ገጸ በረከት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡በመድረኩ መሳተፍና አቅምን ማሳየት በአውሮፓ ሃገራት ባሉ ክለቦች የመታያ ትልቁ አመራጭ ነው፡፡

ታዲያ ባለ ታሪኩ ምንም እንኳ ለመድረኩ መስፈርቱን ቢያሟላም ኢትዮጵያ በወንዶች ኤሊት ዘርፍ ከበጀት ጋር በተያያዘ 3 ብስክሌተኞችን ብቻ ለማሳተፍ ስትወስን ሌላ ጭለማ ተደቀነበት፡፡
ይህንን የልጅነት ህልም እውን ለማደረግ ቀን ከሌሊት አማራጮችን ለማየት ታተረ፡፡
አሁን ካለበት ክለቡ ለኪሱ 4 ሺ ብር ብቻ ሚያገኘው ተስፈኛው ጋላቢ ከመቀለ – አዲስ አበባ -ከአዲስ አበባ ሞምባሳ የአየር ትኬት ክፍያን ሳይሰለች በተማጸናቸው ተቋማትና ግለሰቦች አማካይነት በራሱ ጥረት ኬኒያ ገባ፡፡
በወቅቱ ከ108 ጋላቢዎች መካከል በአዋቂዎች 7ኛ ከ23 አመት በታች ደግሞ 4ኛ ሆኖ በብቃት አጠናቋል፡፡4 ሰዓታት ያህል በክዋሌ ካውንቲ ሰማይ ስር እጅግ ከባድ የሆነውን ውድድር ወድቆ ተነስቶ ከትላልቅ ፕሮፌሽል ጋላቢዎች ጋር ተፋልሞ አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውድድር አደረገ፡፡
ከአጠቃላይ ጋላቢዎች 50ዎቹ ብቻ ባጠናቀቁበት መድረክ እሱና ሌሎች 3 ኢትዮጵያውያን ወድቀው ተነስተው ከ12ኛ በላይ ማጠናቀቃቸው ብቃታቸውን ማሳያ እንደሚሆን አሳማኝ ምክንያት ነው፡፡
ይህ ብላቴና በራሱ ወጪ ሃገርን በአህጉራዊ መድረክ ሲያስጠራ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ቢሆንም መሰራት እንዳለበት የሚያስተምር ክስተትም ሆኖ አልፏል፡፡

ፌደሬሽኙ ለውድደር አድል ስለሰጠው ምስጋናውን የሚያቀርበው አማኑኤል በኢትዮጵያ ብቃት ያለቸው ስፖርተኞች መኖራቸውን በመጠቆም የተሻለ ዝግጀት እና የስነ ልቦና ስልጠናዎች ከተዘጋጁ ከአፍሪካ ምርጥ የማንሆንበት ምክንያት የለም ይላል፡፡
ለዚህ በማሳያነት የከተማና ጎዳና ውድድር የሆነውንና የ163.8 ኪ.ሜ ውድድር እንደ ደቡብ አፍሪካ ፣ አልጄሪያ ፣ ኤርትራ ፣ ሩዋንዳና መሰል ብሄራዊ ቡድኖች 8 ተወዳደሪዎችን በማሳተፍ ሲተጋገዙ እነ አማኑኤል በቁጥር 50 በመቶ አንሰው መሳተፋቸው ለውጤቱ ያለውን የቁጥር አስተዋጾ በማሳየት አስረድቷል፡፡
ብስክሌት የተለየ ማንነት የሚጠይቅ ፣ የአለማ ጽናት የሚያስፈልገው ስፖርት ነው፡፡ ይህንን እውን ለማድርግ አህጉራዊ ውድድሮች ላይ መሳተፍ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ የተቻላቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው ለሌሎች ብስክሌተኞችም ምክሩን ይለግሳል፡፡
የውድድር እድልን መጠቀም ትልቅ ትርጉም ስላለው ብዙ መሰዋትነትን እንደሚከፍሉም ያስረዳል፡፡አማኑኤል ለሃይማኖት ቅርብ የሆነ በጉልበቱ በላቡ ለመኖር የሚጥር ሩቅ አላሚ ስፖርተኛ ነው፡፡በቀን ከ7-8 ሰዓት ልምምድም ያደርጋል፡፡

ባለፉት 7 አመታት በብስክሌት ስፖርት ህይወቱ ብዙ ውጣ ውረዶችንም አሳልፏል፡፡ 3ቱን የፊት ጥርሶቹን በስፖርቱ አማካይነት ያጣው አማኑኤል በቁጥር የማይገለጽ ጠባሳ ሰውነቱ ላይ እንዳለ ይገልጻል፡፡
ኢትዮጵያ ለስፖርቱ ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ገጸ በረከት ያላት እንደሆነ የዩኒቨርሲቲ ሙሁራኖች አረጋግጠዋል የሚለው አማኑኤል ቀደም ሲል በባህር ዳር እና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የነበሩ መነቃቃቶች ወደ ቀድሞ እንዲመለሱ ያሉ ጅማሮዎችን ያደንቃል፡፡
በተለይ በድሬደዋ 4 ክለቦች መኖራቸውን የሚያነሳው አማኑኤል በሌሎች አካባቢዎችም ተኩረት ተሰጥቶበት ፤ በስፖርቱ ያለፉትን ወደ አመራርነት በማምጣት ኢትዮጵያን በስፖርቱ ከፍ ማድረግ ከባድ እንዳልሆነም ይገልጻል።
አማኑኤል ተክለሃይማኖት በቀጣይ ዓመታት በዓለም ትልልቅ ውድድር ላይ መሳተፍ ህልሙ ነው፡፡በተለይ እንደ ቱር ደፍራንስ ያሉ ውድድሮች ላይ ለማሳተፍ በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ነጥቦችን መሰብሰብ ያስፈልጋል ይላል፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ የሚሆነው ቅድሚያ ለስፖርተኛው ትኩረት ከተሰጠው አንደሆነ በአጽንኦት ይገልጻል፡፡
በዮናስ ሞላ