የካሜሩን ቴሌኮሙኒኬሽን (CAMTEL) እና ኢትዮ ቴሌኮም በካሜሩን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማፋጠን የሚያስችል የኮንትራት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን በካሜሩን ያውንዴ በመገኘት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የካምቴል ዋና ስራ አስኪያጅ ጁዲት ያህ ሰንዴይ ፈርመዋል።
የሁለቱ ተቋማት ስምምነት(Master Service Agreement) የካምቴል ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2025 በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተጀመረውና ዕውን የሆነው የትብብር ግንኙነት አካል መሆኑም ተገልጿል።
በወቅቱም የካምቴል አመራሮች ኢትዮ ቴሌኮም የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ” ሀገራዊ አጀንዳን በማፋጠን ረገድ የተጫወተውን ወሳኝ ሚና በመመልከት በካሜሩን ተመሳሳይ ዲጂታል ስኬቶችን ለመተግበር ፍላጎታቸውን ገልጸው ነበር።
የካምቴል ስትራቴጂካዊ ዓላማም የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል መቀየር፣ አካታች የዲጂታል ፋይናንስ መፍትሄዎችን ዕውን ማድረግና የገመድ አልባ ኔትወርክን ማዘመንን ያካተተ መሆኑም ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

ይህንን ራዕዩን ለማሳካትም ካምቴል ኢትዮ ቴሌኮምን ስትራቴጂያዊ አጋር ባደረገበት የትብብር ማዕቀፍ አማካኝነት የካሜሩንን የለውጥ ጉዞ ለማገዝና የካምቴል ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ የአማካሪነት አገልግሎትና የልምድ ልውውጥ ተሞክሮዎችን በማቅረብ በዘርፉ አብሮ የመስራት ዕድልን ያመቻቻል ተብሏል።
ይህ ስምምነትም በዋናነት የሞባይል ገንዘብ ኢኖቬሽን የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ በ”ብሉ መኒ” የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት በጋራ መስራትን ጨምሮ የህዝብ አገልግሎቶችን ዲጂታል ማድረግና ብሄራዊ የመንግሥት ክላውድ(Government Cloud) እንዲቋቋም መደገፍን ያካትታል።
በተጨማሪም የአራተኛውና አምስተኛው ትውልድ(የ4G እና 5G) ኔትወርክና አዳዲስ መፍትሄዎችን ማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ድጋፍን ጨምሮ ተቋማዊ ለውጥን በዋናነት የመረጃ ሥርዓቶችን በማዘመን፣ ደንበኛ-ተኮር ባህልን በማጎልበት ረገድ ድጋፍ በማድረግ የካምቴልን ተቋማዊ ሽግግር ማገዝ መሆኑም ተገልጿል።
ስምምነቱም ካምቴል የካሜሩንን ዲጂታላይዜሽን በማፋጠን አካታች ኢኮኖሚ የመገንባት አቅሙን ሲያጎለብት ኢትዮ ቴሌኮም ‘ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ’ መሰረት ከአፍሪካዊ ኦፕሬተሮች ጋር በአጋርነት የዲጂታል አፍሪካን ጉዞ ለማፋጠንና ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ይከፍታል።