የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሰጠ ነው

You are currently viewing የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሰጠ ነው
  • Post category:ፖለቲካ

‎AMN – ሕዳር 26/2018 ዓ.ም.

‎የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ሁሉንም ወገት አሸናፊ ያደረገና ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሰጠ መሆኑን የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራር አባለት ገለጹ።

‎በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነትና አስተባባሪነት የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተፈርሟል።

‎የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የምትገልጸውን የአፍሪካን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት መርህ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል ።

‎በሁለቱ ወገኖች የተፈረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነትም አለመግባባቶችን ሁሉንም ወገን አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ በድርድርና መነጋገር ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑም ገልፀዋል ።

‎የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ አለመግባባቶችን በውይይትና ድርድር መፍትሔ መስጠት የሰለጠነ ፖለቲካ ሥርዓት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረሰው የዘላቂ ስምምነትም ሰላምን የሚያጸና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

‎የዘላቂ ሰላም ስምምነቱም የውጭ ሃይሎችን ሴራን በማክሸፍ ህዝብ የልማት ሥራውን የሚያፋጥንበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

‎ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ የአፍሪካ ሕብረትና ኢጋድ ለዘላቂ ሰላም ስምምነቱ መፈረም ያደረጉትን አስተዋጽኦም አድንቀዋል።

‎በቀጣይም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አፍሪካ እንደ አህጉር ሁለንተናዊ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የዕድገት ጉዞን ለማደናቀፍ የማይሸረብ ሴራ እንደሌለ ሁሉም መገንዘብ እንደሚገባው ተናግረው፤ ሁላችንም ለሰላም መትጋት አለብን ብለዋል።

‎የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በበኩላቸው፥በአማራ ክልል መንግስት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) የተደረሰው ዘላቂ ስምምነት ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ጥሪ መልስ የሰጠ አስደሳች ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

‎የአፋህድ የሰላም አማራጭ ቁርጠኝነት ለአማራ ህዝብ እፎይታን የሰጠና በትጥቅ ትግል ለሚገኙ ኃይሎችም ትምህርት የሚሰጥ በአርዓያነት የሚወሰድ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

‎በሰላም ስምምነት ሂደቱ የተደረገው ውይይትና ድርድርም ሁሉንም ወገን በእኩልነት አሸናፊ ያደረገ፤ ለዜጎች የሰላም ፍላጎት ምላሽ የሰጠ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በቀጣይም ሌሎችም የሰላማዊ ፖለቲካ ትግልን ተቀዳሚ አማራጫቸው ሊያደርጉ እንደሚገባም ተነግሯል።

‎የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደረግ መቆየቱም ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review