“በዚህ ዓመት ከያዝናቸው ዋነኛ እቅዶች መካከል ቀዳሚው ለከተማችን ነዋሪዎች የቤት አቅርቦትን
ተደራሽ ማድረግ ነው”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
በፍጥነቱ፣ በጥራቱ እና በጥንካሬው ተመራጭ የሆነውን ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ቴክኖሎጂን በመጠቀም የ26 ሺህ ቤቶች ግንባታ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ውበት እንደጅረት የሚጎርፍባት ግሩም ከተማ ናት። ለመኖሪያ፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለመዝናኛ ምቹ በመሆኗ በርካቶች ይመርጧታል፡፡ እናም፣ ከተማዋን በስራ መግቢያና መውጪያ ላስተዋላት ወዲያ ወዲህ የሚተራመሰው የአዳም ዘር መብዛቱን ይገነዘባል፡፡ ከተማዋ ለዚህ ሁሉ ወፈ ሰማይ ምቹ ብትሆንም የቤት ችግር ግን የነዋሪዎቿ ራስ ምታት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ከሰሞኑ በህዝብ አውቶቡስ ላይ ያስተዋልኩትን አንድ እውነት ላጫውታችሁ፡፡ ሁለት በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ስለ ቤት ችግር እያወጉ ነው፡፡ አንደኛው አዛውንት “እንዴት ሰው እግር የማታዘረጋ ቤት አስር ሺህ ብር ያከራያል! መውደቂያ ያጣው ‘ልክፈል’ ቢል እንኳ ህሊና እንዴት ችሎ ዝም ይላል” አሉ፤ ንዴትና ቁጭት ውስጣቸውን እንደናጠው ፊታቸው እያሳበቀባቸው፡፡ ሌላኛው ቀጠል አደረጉና “ለመረዳዳት፣ ለመተሳሰብ ችግራችንን በጋራ ለመካፈል የምንቆምበት የህሊና ምርኩዛችን ከተሰበረ ቆየ” ሲሉ ከኋላቸው የነበሩ ሌላኛው “ጎልማሳ ኧረ እንደቤተሰብ የሚያስቡ አከራዮችም አሉ!” በማለት ጨዋታውን ተቀላቀሉ፡፡ እኔ ግን የቤት ኪራይ ያማረራቸው አዛውንት የችግሩን ክብደት “የህሊና ምርኩዛችን ተሰበረ” በማለት የገለፁበትን መንገድ እያብሰለሰልኩ ወረድኩ፡፡
በእርግጥም የቤት ችግር ተከራዩን እጅጉን ያማረረ ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሰፊ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የችግሩ ስፋት በሚጠይቀው ፍጥነትና ብዛት መጓዝ ባለመቻሉ የቤት እጥረት የከተማዋ ነዋሪዎች ቋሚና አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ስለመቀጠሉ ምስክር አያሻውም፡፡

በእርግጥ የቤት ችግር የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ዓለም በእጅጉ እየተፈተነባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ ጥቅምት 20 ቀን 2023 በኒው ዮርክ ከተማ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የቤት ችግር ማቃለል በሚቻልባቸው ዘዴዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ጥናት በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ጥናታዊ ሪፖርት መሰረትም በዓለማችን ቤት መስራት አሊያም መግዛት የማይችሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመኖሪያ ቤት ወጪያቸውን መክፈል ባለመቻላቸው ብቻ ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ፣ ይህም ለቤት እጦት መባባስ አስተዋጽኦ ስለማድረጉም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ህዝብ በቂ የመኖሪያ ቤት እና መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሌለው የጠቆመው ሪፖርቱ ይህም በ2030 ወደ 3 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በቀረበው የባለሙያዎች ጥናታዊ ሪፖርት መሠረት፣ አስተዳደሮች፣ መንግሥታዊ ድርጅቶች እና ተቋማት የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመፍታት የበለጠ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
አዲስ አበባ ከተማም የተለያዩ የቤት አማራጮችን ለነዋሪዎቿ በማመቻቸት የቤት ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ናት፡፡ ይህንንም ተግባር የበለጠ በሚደግፍና ጥራትና ፍጥነት የታከለበትን የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም እንደ ሀገር አዲስ የሆነውን እና ዓለም በስፋት እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጋለች፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስም (ህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም) የ26 ሺህ ቤቶች ግንባታ ለሀገራችን የመጀመሪያ በሆነ የግንባታ ቴክኖሎጂ በላፍቶ ሳይት ስራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አብስረዋል፡፡
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዚህ ዓመት ከያዝናቸው ዋነኛ እቅዶች መካከል ቀዳሚው ለከተማችን ነዋሪዎች የቤት አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህ ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት አቅደን በርካታ ተግባራትን እያከናወንን ሲሆን፣ እቅዳችንን በጥራትና በፍጥነት እውን ለማድረግ ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) የግንባታ ቴክኖሎጂን መጠቀም አንድ አማራጭ አድርገናል ብለዋል ከንቲባዋ፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ በሌላው ዓለም የተለመደ ሲሆን፣ ህንፃዎችን በፋብሪካ ውስጥ የሚገጣጠሙ ብረቶችን በመጠቀም ወለልን፣ ግድግዳና ጣሪያን ጨምሮ ሁሉንም ክፍል በፍጥነትና በጥራት ማምረት የሚያስችል አሰራር ነው።
የቴክኖሎጂ ፋብሪካው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መተከሉን ገልፀው፣ በፈጠራና ፍጥነት መርህ ግንባታን ከሳይት ወደ ፋብሪካ በመቀየር የግንባታ ፍጥነትን በማሳደግ፣ ወጪን በመቀነስና ጥራትን ከማሻሻል አንጻር ተመራጭ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አስተዳደሩ የነዋሪውን ጥያቄ ለመመለስ እና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በጠንካራ የፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ዲስፕሊን እና በ24/7 የስራ መርሃ ግብር ፕሮጀክቱ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቅቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ያደርጋልም ብለዋል።
ዓለም የቤት ችግርን በፍጥነትና በጥራት ለመቅረፍ እየተጠቀመበት ያለውና አዲስ አበባ ለሀገራችን ያስተዋወቀችው ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) በፍጥነት በሚለዋወጠው የግንባታ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቤት ገንቢዎች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።
ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) የላቀ ጥምረትና ጥንካሬ፣ ዘላቂነት ያለው፣ እሳትን በተሻለ መልኩ መቋቋም የሚችል፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን እና በአውሎ ንፋስ ምክንያት ሊመጣ የሚችልን ችግር መቋቋም የሚችል እና ቆሻሻን በእጅጉ የመቀነስ አቅም አለው ይላል የሳይቤሪያ ስቴት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ ሐምሌ 22 ቀን 2024 የኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡
ቴክኖሎጂው የስራ ጫናን ያቃልላል፣ ወጭን እና ብክነትን ይቀንሳል። ከህንፃ መረጃ ሞዴሊንግ እና ከኮምፒዩተር ዲዛይን ሶፍትዌር ጋር ያለምንም እንከን ይዋሃዳል፤ ይህም ውስብስብ የስነ ህንፃ መዋቅሮችን በትክክል ለማምረት ያስችላል።

ቴክኖሎጂው ሀብትን፣ ጊዜን እና ቦታን በአግባቡ መጠቀም ስለሚያስችል የሀገርን ኢኮኖሚ የመደገፍ አቅም አለው። ለአብነትም አስቀድሞ በፋብሪካ የተሰሩ የኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ክፍሎችን በግንባታ ቦታው ላይ ለመገጣጠም ዝግጁ ሆነው ይደርሳሉ፤ ይህም የሰው ኃይል ወጪን እና የቁሳቁስ ብክነትን ይቀንሳል።
ከእንጨት በተለየ መልኩ ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ለማድረቅ ጊዜ አይፈልግም፤ በመበላሸት ወይም በተባይ ጉዳት ምክንያት ምንም ብክነት አያስከትልም፡፡ በሌላ በኩልም ለረጅም ጊዜ መቆየት ከመቻሉም በላይ ከፍተኛ ብክነትን ከሚያስከትሉት ኮንክሪት እና እንጨት በተቃራኒ ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) በጥቂት ጥገና ብቻ መቶ በመቶ እንደገና ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ነው፡፡
ከእንጨት በተለየ መልኩ፣ ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) አይቃጠልም፣ አይበላሽም፣ አይበሰብስም፣ ምስጦችን አይስብም ይላል የሳይቤሪያ ስቴት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ የኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች በሚል ርዕስ ያሳተመው ፅሑፍ፡፡
በፅሑፉ በግልፅ እንደሰፈረው በዘመናዊ የግንባታ ሂደት ውስጥ፣ ዘላቂ፣ ሁለገብ እና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቁሳቁሶች በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ በዚህም ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) በዓለማችን ግንባታ አንዱስትሪ ውስጥ እጅጉን ተመራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡
ከኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ዋና ዋና ጥቅሞች አንዱ አስደናቂ የጥንካሬ እና የክብደት ጥምርታው ነው። ቀላል ክብደት ያለው ቢሆንም በልዩ መዋቅር የተሰራ በመሆኑ ጥንካሬው አስተማማኝ ነው፡፡ በቀላል ክብደቱ ምክንያትም ለመያዝ እና ለማጓጓዝ አያስቸግርም፤ ይህም የማጓጓዣ ወጭን እና የቦታ አስተዳደርን ቀላል ያደርገዋል። በጥገና ምክንያት የሚባክን ጊዜና ገንዘብንም ይቀንሳል ይላል የዩኒቨርሲቲው ጥናታዊ ፅሑፍ።

የኮንስትራክሽን ኢንጅኒዬር በሱፈቃድ አየለ እንደሚሉት ዓለም አቀፉ የግንባታ ዘርፍ ለከፍተኛ የኃይል ፍጆታ እና ከኃይል ጋር ለተያያዘ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀቶች ተጠያቂነትም፣ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ያሉ ከተፈጥሮ የሚስማሙ፣ ፈጣን፣ ወጭ ቆጣቢ እና አስተማማኝ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አንፃር ክፍተት በመኖሩ በዘርፉ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡
ዓለም በስፋት በተለይም ያደጉት ሀገራት እየተጠቀመበት ያለውን ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ቴክኖሎጂን አዲስ አበባ መጠቀም መቻሏ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ለአብነትም በከተማዋ የሚስተዋለውን የቤት አቅርቦት ችግር በፍጥነት፣ በጥራትና ሁለንተናዊ አስተማማኝነትን ባረጋገጠ መልኩ ችግሮቹን በሂደት መፍታት ያስችላል፡፡
ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው ይህ ቴክኖሎጅ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጅ ምጥቀት ጋር በማስታረቅ፣ የጊዜን እና የገንዘብን ብክነትን በመቀነስ ይባክኑ የነበሩ ሀብቶቻችንን በሌሎች ልማቶች ላይ በማዋል የሀገርን ከፍታ ማፋጠን ያስችላል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ በስፋት እየሰራችበት ካለው እና ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ካስገኘላት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ወይም በከተማ እና በገጠር መልክዓ ምድሮች ላይ ችግኞችን በመትከል ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ደህንነትን እና ሥነ-ምህዳርን በማሻሻል የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ማሳደግን መሰረት ካደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር የሚጣጣም በመሆኑ ኮልድ ፎርምድ እስቲል (ሲ.ኤ.ኤስ) ፋይዳው ከቤት አቅርቦትም በላይ መሆኑን የኮንስትራክሽን ኢንጅኒዬሩ ገልፀዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ