የሕገ-መንግስት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያውያንን አብሮነት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል መሰራት ካለባቸው የቤት ስራዎች መካከል የወል ትርክት ግንባታ አንዱ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዘንድሮ ለ20ኛ ግዜ ይከበራል፡፡ ቀኑን ለወል ትርክት ግንባታ አጋዥ በሆነ መልኩ ለማክበር መስራት ያስፈልጋል፡፡
የመጣንበት መንገድና ውስንነቶቹ
የሕገ-መንግስት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ስርዓት ነጠላ ትርክት ላይ መሰረቱን የጣለ አካሄድ ይከተል ነበር፡፡ በነበረው ሂደት የተፈጠረው ትልቁ ችግር ብዝሃነትን በአግባቡ ማስኬድ አለመቻሉ ነበር፡፡ ብዝሃነት በውስጡ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖትና መሰል ጥብቅ ጉዳዮቻችንን የሚይዝ ነው፡፡ ይህንን በአግባቡ አስተናግደናል ብሎ ለማለት አያስደፍርም፡፡
ብዝሃነትን ለማስተናገድ የግድ መሬት ላይ ወርዶ ተፈፃሚነትን ያተረፈ የአሰራር ስርዓት መከተል ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት ይስተዋል የነበረውን ነጠላ ትርክትን በማረቅ የወል ትርክትን ለማስረጽ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኃይለየሱስ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ብዝሃነታችን የህብረ ብሔራዊነታችን መገለጫ ሆኖ ሳለ ያስተናገድንበት መንገድ ግን ነጠላ ትርክትን በሚያሰርፅ አግባብ ነበር፡፡ ወደራስ ያተኮረ የብሔር ማንነት ላይ ብቻ ትኩረቱን በማድረግ ነጣጣይ ትርክት ላይ ያተኩር ነበር፡፡ ከጊዜ ቆይታ በኋላም በጋራ አብሮነታችን ላይ ጫና በመፍጠሩ ምክንያት ዋጋ የከፈልንባቸው ነገሮች አሉ፡፡
“ነጠላ ትርክት ሀገር በሁለት እግሯ እንዳትቆም ያደርጋል” የሚሉት ኃይለየሱስ (ዶ/ር)፣ “የፌዴራል ስርዓቱ ተመሰረተ፣ ህገ መንግስቱ ወጣ፣ ክልሎች ተደራጁ” ይባል እንጂ ከዚያ ያለፈ አተገባበሩ ላይ የተጨነቀ አልነበረም፡፡ የፌዴራል ስርዓት ፍልስፍናው አብሮነት ስለመሆኑ ተገቢውን መረዳት ማህበረሰቡ ዘንድ እንዳልነበረ አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው ስርዓት በየጊዜው ለሚነሱ ጥያቄዎችና ችግሮች ከስር ከስር መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ አድበስብሶ እና ትኩረት በመንፈግ ሂደቶችን እንደ አስፈላጊነታቸው ያስቀጥል ነበር፡፡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ህብረ ብሔራዊነት ለማስጠበቅ የተዘጋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያና ህጎችን በአግባቡ ተፈፃሚ ለማድረግ የተሰራ ስራ አለመኖሩን ጭምር ኃይለየሱስ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡ በተለይም የፌዴራል ስርዓቱ በራሱ የተገነባበት ትርክት አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን እርስ በእርስ የሚያጋጭ፣ የሚበታትን ሴራን መሰረት ያደረገ እና ሀገርን ከማቅናት ህዝቦችን ከማወዳጀት ይልቅ ትኩረቱን ነጠላ ትርክት ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በሚል የተለያዩ መልዕክቶች ተቀርፀው ይከበራሉ፡፡ መልዕክቶቹ በትክክል ዓላማቸው ምን እንደሆኑና ለምን እንደሚከበሩ በግልፅነት የተቀመጠ ነገር አልነበራቸውም ሲሉም አክለዋል፡፡
ማህበረሰቡ በዓሉን የተረዳበት መንገድ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ከዚህ ቀደም ይከበር የነበረበት አግባብ ብሔርተኛነትን በማጉላት አንደኛውን ብሔር ከሌላኛው ጋር የሚያራርቅ ነበር የሚሉት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ነዋሪ አቶ ሃይሉ ጉተማ ናቸው። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ተብሎ ይከበር እንጂ እርስ በእርስ ያለንን ህብረ ብሔራዊነት ከማንጸባረቅ ይልቅ ግለኝነትን በሚያዳብር ተግባራት የታጀበ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሀገራዊ ለውጡ ህብረ ብሔራዊነትን ያስከበረ፣ የብሔረሰቦችን ማንነት ከፍ ያደረገ እና አንዱን ከአንዱ እኩል ለማስተናገድ የሚያስችል የፌደራሊዝም ስርዓት ማስፈን ያስቻለ ብሎም የጋራ ትርክታችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ መንገዱን ያሳየ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ወይዘሮ ትነበብ ንጉሴ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ነው፡፡ ከለውጡ በፊት በነበረው ስርዓት በህገ መንግስት ደረጃ የጸደቁ መመሪያዎች እና ደንቦች በርካታ ቢሆኑም ከተፈፃሚነታቸውና በአግባቡ መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ክፍተት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአይነ ቁራኛ እንዲተያዩ፣ አንዱ የአንዱ ጠላት እንደሆነ እንዲያስብ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የጋራ ትርክት ላይ መሰረቱን የጣለ ስራ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ትነበብ ገለፃ፤ ከለውጡ ማግስት የተናጥል ትርክትን ወደ ወል ትርክት ለማምጣት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን በህብረ ብሔራዊነታችን ውስጥ ያለውን የደመቀ ማንነታችንን ለወል ትርክት ማጠናከሪያነት መጠቀም ይኖርብናል ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ወዲሾ ህዳር 29 የሚከበረውን 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን አስመልክቶ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት ይስተዋል የነበረውን የነጠላ ትርክትን በማረቅ የወል ትርክትን ለማስረጽ የቀኑ መከበር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓትን መከተል ከጀመረች ከሰላሳ ዓመት በላይ ያስቆጠረች ቢሆንም በብሔር ማንነት፣ በባህልና በቋንቋ ላይ ትኩረት ያደረገና ነጠላ ትርክትን የሚያጎላ እንደነበር አስታውሰዋል።
እንደ አቶ በላይ ገለፃ፤ በዓሉ በሕዝቦች መካከል ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እና ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል፡፡
ለወል ትርክት ግንባታ ምን መንገድ እንከተል?
የጋራ ጉዳያችን በፌዴራል ስርዓት እሳቤ ሲመነዘር የወል የሚያደርጉን ጉዳዮች ጎልተው እንዲወጡ ማስቻል እንደሆነ የሚናገሩት ኃይለየሱስ (ዶ/ር)፣ የህብረ ብሔራዊነታችን መገለጫዎች በርካታ ናቸው፡፡ በህብረት ስንሆን እንዋባለን፤ ጠላት የማይደፍረን ብርቱ የታሪክ ባለቤቶች እንድንሆን ያደርገናል፡፡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በሚከበርበት ወቅት አንዱ የአንዱን የአኗኗር ዘይቤ በመረዳት ብሎም በማክበር የሚያጋምደንን ፍቅር በማጎልበት የወል ትርክት ባለቤቶች እንድንሆን ያደርገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃይለየሱስ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ሀገራችን በተፈጥሮ ሃብት እጅግ የታደለች፣ በርካታ ቁጥር ያለው የሰው ሃይል ያላት አቅሟን በበርካታ መንገድ ስንፈትሸው የያዘቸው መንገድ አዋጭ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ አቅሞች የወል ትርክታችን እንዲሆኑ ማድረግ ድህነትን የማሸነፍ ሙሉ አቅም ለመፍጠር ያስችለናል፡፡
ህብረ ብሔራዊነት ብሎም አንድነት ላይ መሰረቱን የጣለ የፌዴራሊዝም ስርዓት በአግባቡ መሬት ላይ እንዲተገበር የሚቀረጹ መልዕክቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኃይለየሱስ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን ስናከብር የመርሃ ግብሮች ማጠንጠኛ የወል ትርክት ማስረጽ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም መልዕክቱን ተደራሽ ለምናደርገው አካል ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሰረት በህገ መንግስትና በፌዴራሊዝም ስርዓት ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠሪያ መድረኮች ተዘጋጅተው ቀደም ብሎ እውቀቱን እንዲገኝ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል። የአመለካከት ችግር ከመቅረፍ አንፃርም ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡
እንደ ኃይለየሱስ (ዶ/ር) ገለፃ፣ ከአንድ ወር በፊት በህገ መንግስትና በፌዴራሊዝም ስርዓት ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብሔር ብሔረሰቦች ሲገናኙ ስለራሳቸው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለ ጋራ ጉዳያቸው ጭምር እንዲወያዩ ማስቻል ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ስያሜ የተሰጣቸው አምስቱ ቀናትን በተመለከተ ከህዳር 25 እስከ 29 ድረስ የወንድማማቾች ቀን፣ የአብሮነት ቀን፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቀን፣ የምክክር ቀን፣ የኢትዮጵያውያን ቀን በሚል በድምቀት እየተከበሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን