እንሰት ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከምግብ በላይ የክልሉ ብሔረሰቦች መለያ ዓርማ ነው።
ይህ ልዩ ተክል በክልሉ ያሉ 10 ብሄረሰቦች መገለጫ ይሆን ዘንድ 10 ቅጠሎችን የያዘ የእንሰት ሃውልት በወልቂጤ ከተማ መግቢያ ላይ ተሰርቷል።
ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጐች ለምግብነት የሚጠቀሙበት እንሰት የክልሉ ህዝቦች አንድነት እና ትስስር መገለጫ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገልፀዋል።
የእንሰት ተክልን በሃገር እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በተሰራው ስራ በዓለም የምግብ ዘርፍ ውስጥ መያዙንና በቀጣይ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለምግብነት እንዲጠቀምበት እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት።
ስለሆነም እንሰትን በክልሉ በሚከበረው 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ለተቀረው የሃገሪቱ ብሔረሰቦች የምናስተዋውቀው ሃብት ነው ብለዋል።
በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ለማስተዋወቅ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው ጉራጌ የሚታወቅበትን የክትፎ ምግብ ጨምሮ የጊቤ ፓርክ እና ዘመናዊ የቤት አሰራር የሆነውን ጀፎረ የማስተዋወቅ እና የማልማት ስራ እየተሰራ ነዉ፡፡
በተለይ ጀፎረን ለዓለም ለማስተዋወቅ እና በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በያለው ጌታነህ