የሊጉን ዋንጫ የማንሳት አቅም እንዳለው በበርካቶች የተመሰከረለት አርሰናል ዛሬ ፈታኙን ጨዋታ ያደርጋል።
መድፈኞቹ በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር አስቶንቪላን ይፋለማሉ።
ቀን 9:30 በቪላ ፓርክ የሚደረገው ጨዋታ የላቀ የታክቲክ እውቀት ያላቸው ሁለቱ ስፔናውያን አሰልጣኞች የሚያደርጉትም ፍልሚያ በመሆኑ በጉጉት ይጠበቃል።
የአስቶንቪላው አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬይ የዘንድሮ ውድድር ዓመት አጀማመራቸው የወረደ ነበር። ቪላን ከተረከቡ በኋላ አስከፊውን የውጤት ማጣት ቢጋፈጡም ማንም ብቃታቸውን እንዳይጠራጠር አድርገው ቡድኑን ወደ ቀድሞ ተፎካካሪነቱ መልሰውታል።

ቪላ በመጀመሪያዎቹ አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስቆጥር ሁለቱን አቻ ወጥቶ ሁለቱን ተሸንፎ ቢጀምርም አሁን ላይ ከዛሬ ተጋጣሚው አርሰናል በስድስት ነጥብ ብቻ አንሶ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኡናይ ኤምሬይ በቂ ጊዜ ሳይሰጠኝ አሰናብቶኛል የሚሉት የቀድሞ ክለባቸው አርሰናልን ካሸነፉ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሌላ እጥፋት መፍጠራቸው አይቀርም። አርሰናል ከሊጉ ክለቦች የተሻለ ወጥነት እያሳየ ይገኛል። ከመጨረሻ 10 የሊግ ጨዋታዎቹ ሰባቱን አሸንፎ በሦስቱ አቻ ተለያይቷል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በነሃሴ ወር መጨረሻ በአንፊልድ በሊቨርፑል ከተሸነፈ በኋላ ለየትኛውም ቡድን እጅ አልሰጠም። አርሰናል ምንም እንኳን አስተማማኝ ብቃት ላይ ቢገኝም የዛሬው ተጋጣሚው ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት አሳይቶታል።
በ2023/24 የውድድር ዓመት የማይቀመስ የሚመስለውን የአርሰናልን ጉዞ ከገቱ ቡድኖች አንዱ አስቶቪላ ነበር። በውድድር ዓመቱ ቪላ ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፉ ይታወሳል።
ባለፈው የውድድር ዓመትም በኤምሬትስ 2ለ2 መለያየታቸው ሊቨርፑል ዋንጫ እንዲያነሳ መንገዱን ጠርጓል። በእርግጥ የሚካኤል አርቴታው ቡድን በታሪክ አስቶንቪላ ላይ ያለው የበላይነት ከፍተኛ ነው።

በፕሪምየር ሊግ 48 ግንኙነት አርሰናል 30 ሲያሸንፍ ቪላ ድል የቀናው በስምንቱ ብቻ ነው። አርሰናል ይህን የበላይነቱን መስቀጠል የዛሬ አላማው ነው። ያደርገው ይሆን? ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የሚጀምረው ጨዋታ ምላሽ ይሰጠናል።
በሌሎች የሊጉ ጨዋታዎች በሊድስ ዩናይትድ ተሸንፎ ከዋንጫ ፉክክሩ ራቅ ያለው ቼልሲ ከሜዳው ውጪ ቦርንማውዝን ይገጥማል። ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ በኢትሃድ ስታዲየም ብዙሃኑን እያስገረመ የሚገኘው ሰንደርላንድን ያስተናግዳል።
የቶተንሃም አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ የቀድሞ ክለባቸው ብሬንትፎርድ የሚገጥሙበት ጨዋታም ይጠበቃል። ኤቨርተን ከኖቲንግሃም ፎረስት ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከበርንሌይ ሌሎች የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎች ናቸው።
ሁሉም ጨዋታዎች ምሽት 12 ሰዓት ሲል የሚጀምሩ ይሆናል። ምሽት 2:30 አሁንም ከውጤት ማጣት ያልተላቀቀው ሊቨርፑል ወደ ኤላንድ ሮድ አቅንቶ ሊድስ ዮናይትድን ይገጥማል።
በሸዋንግዛው ግርማ