በዛሬው ዕለት ከማለዳ አንስቶ በአዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ-ከተሞች ከነዋሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት መካሄዱን የመዲናዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል።
በውይይት መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው ከንቲባ አዳነች የገለፁት፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች ላይ ከነዋሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎች እና አስተያየቶች መንግስት በተግባር የሰጣቸውን ምላሾች፣ እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን አስመልክቶ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና ሚኒስትሮች መድረኮቹን በመምራት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ የቤት ስራም ወስደዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ በተለያዩ የልማት ሥራዎች አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡት መንግሥትና ሕዝብ አንድ ሆነው በመቀናጀትና በመናበብ ሊፈጽሟቸው በመቻላቸው መሁኑንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውሰዋል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም “ዛሬም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የተሰሩ በርካታ ሥራዎችን እና የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ እንዲሁም የሕዝብን ተሳትፎ ይበልጥ በሚያረጋግጡ ቀጣይ የጋራ ዕቅዶች ላይ እንደ ወትሮው ከነዋሪዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ያገኘንበት ፍሬያማ የውይይት መድረክ ነበር” ብለዋል።
ውድ ነዋሪዎቻችን፣ ለሰጣችሁን ገንቢ አስተያየት፣ ለነበራችሁ ከፍተኛ ተሳትፎ፣ ለሰጣችሁን ውድ ጊዜ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ያሉት ከንቲባዋ ፤ በቀጣይም ይበልጥ ተቀራርበን መሥራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡