ከለውጡ በኋላ የብሔርና የሀገር ማንነቶች በሚዛን እንዲጓዙ ማድረግ ተችሏል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳእና ከተማ የሚከበረዉን 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል አከባበር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ ከነጠላ ትርክት ይልቅ የጋራ ትርክት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ለክልሉ ሰላምና ልማት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
“ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በክልሉ አስተናጋጅነት እየተከበረ የሚገኘው በዓል፤ የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦች ለማስተሳሰር፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የነበሩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እና ዴሞክራሲያዊ ግንባታን በክልሉ ለማጠናከር ስለማገዙ ተናግረዋል።
ህዳር 29 በሆሳዕና በሚከበረው በዓል ላይ ከ50 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ የገለጹት እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚታደሙ ተሳታፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ይገኛሉም ብለዋል።
በበላይሁን ፍስሃ