ካሜሩን በካሜሩን ቴሌኮሙኒኬሽን (CAMTEL) እና ኢትዮ ቴሌኮም የፈጠሩት ስትራቴጂካዊ ጥምረት ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዲዮን ንጉቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የካሜሩን ቴሌኮሙኒኬሽን (CAMTEL) እና ኢትዮ ቴሌኮም በካሜሩን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማፋጠን የሚያስችል የኮንትራት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን በካሜሩን ያውንዴ በመገኘት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የካምቴል ዋና ስራ አስኪያጅ ጁዲት ያህ ሰንዴይ ፈርመዋል።
የሁለቱ ተቋማት ስምምነት(Master Service Agreement) የካምቴል ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2025 በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተጀመረውና ዕውን የሆነው የትብብር ግንኙነት አካል መሆኑም ተገልጿል።
የካሜሮን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዲዮን ንጉቴ(ዶ/ር) ኢትዮ ቴሌኮም እና ካምቴል የፈጠሩት ስትራቴጂካዊ አጋርነት አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲጂታላይዜሽን የዘላቂ ልማት ምሰሶ መሆኑን ገልጸው ይህም እውን ሊሆን የሚችለው በአፍሪካ የቴሌኮም ተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር ሲኖር ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድም ሁለቱ ተቋማት የወሰዱትን እርምጃ አድንቀዋል።
የካሜሮን መንግስት ለተቋማቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ጥምረቱ በኢትዮጵያ ያለው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በካሜሮንም እንዲደገም ያደርጋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ዲጂታላይዜሽን በማፋጠን አካታች ኢኮኖሚ የመገንባት አቅሙን ሲያጎለብት ኢትዮ ቴሌኮም ‘ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ’ መሰረት ከአፍሪካዊ ኦፕሬተሮች ጋር በአጋርነት የዲጂታል አፍሪካን ጉዞ ለማፋጠንና ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ እንደሚከፍት ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመልክቷል።