ኢትዮጵያ ከተመጽዋችነት ተላቃ የአፍሪካ የስንዴ ምርት ቁንጮ ሆናለች ሲል አሻርቅ ኒውስ ዘገበ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከተመጽዋችነት ተላቃ የአፍሪካ የስንዴ ምርት ቁንጮ ሆናለች ሲል አሻርቅ ኒውስ ዘገበ

AMN – ሕዳር 28/2018 ዓ.ም.

“ለብዙ አሰርት ዓመታት ከረሀብ ጋር ስሟ ተቆራኝቶ የቆየችው ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ የግብርና ለውጥ ስኬት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች” በማለት አሻርቅ ኒውስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት የስንዴ ዕርዳታ መቀበል ማቆሟን በይፋ ካወጀች በኋላ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት በስንዴ ምርት ሙሉ ለሙሉ ራሷን ችላለች ብሏል ሚዲያው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁጥር አንድ የስንዴ አምራች በመሆን ታሪክ ሰርታለች ያለው አሻርቅ መንግሥት በተከተለው የግብርና ፖሊሲ ምክንያት የስንዴ ምርትን በዕጥፍ ለማሳደጉ ሶስት ምክንያቶችን ገልጿል። ከፍተኛ የመስኖ እርሻ መስፋፋት፣ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙ እንዲሁም መንግሥት የምግብ ምርትን የሚደግፍ ፖሊሲ መተግበሩ ይህን አስገራሚ ለውጥ እንዲያመጣ አስችሎታል ብሏል።

ኢትዮጵያ ካላት 112 ሚሊየን ሔክታር መሬት ውስጥ 38 ሚሊየን ሔክታር የሚጠጋው ለግብርና ምቹ መሆኑን በመግለጽ ሀገሪቱ በአግባቡ ከተጠቀመችበት በአንድ የግብርና ወቅት ብቻ 100 ሚሊየን ቶን የሚደርስ ስንዴ የማምረት አቅም አንዳላት ነው አሻርቅ የተነተነው።

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ስንዴ ምርት ከ15 ወደ 24 ሚሊየን ቶን ያደገ ቢሆንም የሀገሪቱ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታ ከ8 ሚሊየን ቶን የሚበልጥ ባለመሆኑ የሚተርፈውን ስንዴ ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደምትችል አሻርቅ ኒውስ በአረብኛ ቋንቋ ዘግቧል።

መቀመጫውን ሳውዲ አረቢያ ያደረገውና ተደራሽነቱን ከአረቡ ዓለም አልፎ በመላው ዓለም ያደረገው አሻርቅ ኒውስ በዋናነት ትኩረቱን በኢኮኖሚ፣ በገንዘብና በዓለም አቀፍ የንግድ ዜናዎች ላይ አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ከብሉምበርግ ጋር አጋርነት በመፍጠር ጭምር የሚሠራ ሚዲያ መሆኑ ይታወቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review