ኢትዮጵያ መልከ ብዙ መሆኗን በመረዳት የጋራ ትርክትን በማስረፅ ለልማት እና ለእድገት መስራት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
ይህንን የተናገሩት 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ሲሆን፣ ትልቁ ሀገራዊ ፈተና ብዝሀነት እያወቁ ተግባራዊ ለማድረግ አለመፈለግ መሆኑን አብራርተዋል።
በሲምፖዚየሙ በበርካታ ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ወቅት “ዴሞክራሲና የፌዴራል ስርዓት”፣ “የምርጫ ስርዓት”፣ “ብዝሐነትና የብዝሐነት አስተዳደር” እንዲሁም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብዝሐነትና ፀጋን የዳሰሱ ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ እና ልማትን ለማረጋገጥ በሀገራዊ የጋራ ትርክት ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሲምፖዚየሙ ሌላኛው ተሳታፊ የሆኑት አረጋዊ በርሄ ዶ/ር ደግሞ ሰላምና አንድነትን ለማስፈን በዴሞክራሲያዊ መግባባት መስራት እንደሚገባና ህዝቦች በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የብሔሮች በዓል ይከበር እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን በዓሉ ትርጉም ባለው መልኩና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ ሁኔታ መከበሩ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ መሆኑን እንደሚያሳይ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ይህንን አዎንታዊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።
ኢትዮጵያን “እንደ ጃንጥላ” አድርገው በመመሰል ያስረዱት ተሳታፊዎቹ፣ ሁሉም የጃንጥላው ክፍል የሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የራሳቸውን ማንነት ከሀገር አንድነት ጋር አዛምደውና አጋምደው ማስቀጠል እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በመሆኑም፣ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ብልፅግናን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑ በሲምፖዚየሙ ላይ የተሰነዘረ ዋና መልዕክት ነበር።
በያለው ጌታነህ