በነገው እለት መላው ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት እና በደማቅ ዝግጅት የሚከበረውን 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ የተለያዩ ዝግጅቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በዛሬው እለት “በምክክር ቀን” ውሎ በሆሳዕና ከተማ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ አራት ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀረበኑ ሲሆን፣ ጥናቶቹ በተለይ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት “ዴሞክራሲና የፌዴራል ስርዓት አተገባበር በኢትዮጵያ”፣ “የምርጫ ስርዓትና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ”፣ “ብዝሐነትና የብዝሐነት አስተዳደር” እንዲሁም ከክልሉ መነሻ “የጋራ እሴቶችና ጸጋዎች ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ያተኮሩ ነበሩ፡፡

የቀረቡትን ጥናታዊ ጹሁፎችን በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወ/ሮ እናታለም መለሰ፣ ሀገር ዴሞክራሲ፣ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም፣ የብዝሐነት አስተዳደርና የምርጫ ስርዓት ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
“ዴሞክራሲና የፌዴራል ስርዓት አተገባበር በኢትዮጵያ” በሚል የጥናት ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ በላይ ወዲሾ፣ የሀገራት የዴሞክራሲ ስርዓት ተሞክሮዎችን አብራርተው አብሮነት፣ በመግባባትና በጋራ ሀገርን መገንባት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ ዴሞክራሲና ብዝሃነትን በአግባቡ የሚያስተናግድ የፌደራል ስርዓት ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር በፖለቲካ ባህልና በጠንካራና ነጻ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት አቶ በላይ፣ ተቀራርቦ የመመካከር፣ የመተሳሰብ ባህልን ማጎልበት ወሳኝ ነው ብለዋል።
“የምርጫ ስርዓትና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ” በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ማዕረጉ በዛብህ በበኩላቸው፣ ከሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የሚነሱ የምርጫ ስርዓቶች ለውጤታማ መንግስታት መመስረትና ውጤታማ መሆን ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) “ብዝሐነትና የብዝሐነት አስተዳደር” በሚል የጥናት ወረቀታቸው፣ በብዝሐነት አያያዝና አስተዳደር ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ልዩነትንና አንድነትን በተጣጣመ መልኩ ማስተዳደር እንደሚገባ የጠቆሙት ምህረቱ (ዶ/ር)፣ ብዝሐነት ምቹ ድምር፣ መልካም እድሎችና ፈተናዎች አሉበት ብለዋል።
ለብዝሐነት አስተዳደር ስኬታማነት የማህበረሰብ ውቅር፣ የጋራ ህልምና የሀገራዊ አንድነት እሳቤ ጉዳዮች መታሰብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም የብሔራዊና የብሔር ማንነትን አጣጥሞ መሄድ እንደሚገባ ምህረቱ (ዶ/ር) አስረድተዋል።
“የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦች የጋራ እሴቶችና ጸጋዎች ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል የጥናት ወረቀት ያቀረቡት አክመል መሀመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የክልሉን ህዝቦች በጋራ ወደ ብልግጽና ሊያሻግሩ የሚችሉ ሀብቶች፣ ጸጋዎችንም ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ አብራርተዋል።
በተለይም የክልሉ ሕዝቦች ሁለንተናዊ ትስስር፣ የሥነ ልቦና አንድነት፣ ስራ ወዳድነትና በርካታ ጸጋዎች ክልሉ ለማዕከል ካለው ቅርበት ጋር ተዳምሮ የለውጥ ማዕከል የመሆን ሰፊ እድል እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ክልሉ የበርካታ የቱሪስት መስህቦችና የልማት አማራጮች ባለቤት መሆኑን በጥናታቸው ገልጸዋ።
አስተያየታቸውን የሰጡ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን በጋራ ሆኖ መደገፍና ዘላቂነቱን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቡድኖች ከሀይል አማራጭ ወደ ዴሞክራሲና ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ተቀራርቦ መነጋገር፣ ህገ መንግስቱን ማስከበር፣ የጋራ መግባባትን መፍጠርና አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ በልዩነቶች ውስጥ ሆኖ ሀገራዊ አንድነትን ማጽናት፣ ፈተናዎችን በጋራ ሆኖ መመከት ወሳኝ እንደሆነ መግለፃቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡