ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበረውን 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በሆሳዕና ከተማ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በበዓሉ ዋዜማ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡
በሲምፖሲየሙ ላይ “ብዝሐነትና የብዝሐነት አስተዳደር” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጹሁፋቸውን ያቀረበት ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር)፣ በብዙ ሀገራት እንደ ችግር የሚስተዋለው ብዝሐነትን እና ብዝሐነትን ማስተዳደር በአግባቡ አለመቻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ብዝሐነትን ለማስተዳደር ጠንካራ የመንግስት ስርዓት መኖር፣ የማህበረሰብ ውቅር ጠንካራ መሆን እና በመደመር መንግስት የመጣ የጋራ ህልም መኖር እንደሚያስፈልግም ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ በብዝሐነት የተከናወኑ አኩሪ ተግባራት መኖራቸውን ያብራሩት ምህረቱ (ዶ/ር)፣ ለአብነትም የዓድዋን ድል ታሪክና የታላቁን ህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ አንስተዋል፡፡
ብዝሐነት መርገምት ሳይሆን በረከት እንደሆነ ያብራሩት ምህረቱ (ዶ/ር)፣ እውነተኛ ብዝሐነት አካታች የሆነና የሁሉንም ቀለማት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ብዝሐነት ሀይል የሚሰበሰብበት፣ በጋራ የሚሻገሩበት፣ እንጂ ሀይል የሚበተንበት እና አንዱ አሻጋሪ፣ ሌላኛው ተሻጋሪ የሚሆኑበት እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
ዓለም በሰላም እንድትኖር ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል አንዱ ብዝሐነትን በአግባቡ የማስተዳደር ጉዳይ በመሆኑ፣ ብዝሐነትን ለማስተዳደር ከራሳችን ሀሳብ በላይ የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን