AMN – ሕዳር 29/2018 ዓ.ም.
የ20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ክብረ በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ኅብረ-ብሔራዊ መልክን በሚያሳይ መልኩ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር በመጠሪያው ልዩ በሆነው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዓሉ መከበሩ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማዕከላዊ ሀሳብ የሆነውን ብሔራዊ መሻት እና ፍላጎት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊነትን “በኅብረ ቀለም የሚሳል፣ በኅብር ባህል የሚኖር፣ በኅብር ቋንቋ የሚነገር፣ በኅብር ደም የተሠራ፣ በኅብር ላብ የሚገነባ እና በኅብር ጥበብ የሚሻገር” በማለት የገለጹት ሲሆን ኢትዮጵያም የነበረች፣ የምትኖር፣ የምትጸናና የማትናወጥ ሀገር መሆኗን በኩራት አስረግጠዋል።

በንግግራቸው ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች የጋራ ውበትና ክብር መሆኗን ለማሳየት የአፋር ዳጉን ለዳውሮ፣ የሲዳማ ጨምበላላን ለአማራው፣ የኦሮሞ ገዳን ለሐረሪ፣ የአክሱም ሐውልትን ለሐድያ፣ የጀጎል ግንብን ለቤኒሻንጉል፣ የፋሲል ቤተ መንግስትን ለሐድያ፣ የሶማሌ ዳንቶን ለጋሞ እንዲሁም የጉራጌ ክትፎን ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሳሌ አድርገው አቅርበዋል።
አንዳችን ለሌላችን ክብርና ውበት የሆንባትን ሀገር በእኩልነትና በወንድማማችነት ተያይቶ፣ በመደመር እሳቤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆች ማሻገር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሀገሪቱ ከተሞቿን እያሸበረቀች፣ ገጠሯን ለመሻገር እየጣረች መሆኑን ገልጸው፣ ታሪካዊ ቅርሶችም አቧራቸውን አራግፈው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት መሆን መቻላቸውን አብራርተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የማዕድንና የቱሪዝም ሀብቶች እየተገለጠና እያበበ እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም እየሰፋ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ያለውን አስተዋጽዖ ተናግረዋል።
በሔለን ተስፋዬ