የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አክሲዮኖቻቸውን ማስመዝገብ ኖሮባቸው እስካሁን ላላስመዘገቡ አክሲዮን ማሕበራት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ማንኛውም ለሕዝብ የሚቀርብ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ለገበያ ከመቅረቡ በፊት በባለስልጣኑ መመዝገብ እንዳለበት አዋጁ በግልጽ የደነገገ ሲሆን፣ ላለፈው አንድ ዓመት አክሲዮን ማሕበራት ምዝገባ እንዲያካሂዱ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል።
በዚሁ ነባር አክሲዮን ማሕበራት ያሏቸውን የሙዓለ ንዋይ ሰነዶች እስከ ሕዳር 16 ቀን 2018 ዓ.ም. እንዲያስመዘግቡ የተሰጠውን ቀነ ገድብ በመጠናቀቁ ምክንያት ያልተመዘገቡ አክሲዮኖችን ለግብይት ማቅረብ እና መገበያየት እንደ ወንጀል ተቆጥሮ አክሲዮን ማሕበሮችን እንደሚያስቀጣ ባለስልጣኑ ለኤኤምኤን በላከው መረጃ ገልጿል።
ባለስልጣኑ እንደገለጸው ባልተመዘገቡ አክሲዮኖች ላይ ግብይት መፈጸም ከ7 እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እና ከ150,000 እስከ 300,000 ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ የሚያስከትል ወንጀል ነው።
ስለሆነም እስካሁን ያላስመዘገቡ አክሲዮን ማሕበራት ከአዲስም ሆነ ነባር አክሲዮን ሽያጭ እና ግብይት ጋር የተያያዘ ማንኛውንም እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በጥብቅ አስጠንቅቋል።
ባለስልጣኑ ማስጠንቀቂያውን ተላልፈው በሚገኙ አክሲዮን ማህበራት ላይ ሽያጮችን መሰረዝን ጨምሮ የኩባንያውን የሥራ ኃላፊዎችና የቦርድ አባላት እስከማገድ እና ጥቁር መዝገብ ላይ እስከማሰፈር ሊደርስ ይችላል።
ኅብረተሰቡም አክሲዮን ከመግዛቱ ወይም ከመገበያየቱ በፊት ድርጅቱ መመዝገቡን ወይም ከምዝገባ ነፃ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ጥብቅ መልእክት ባለስልጣኑ አስተላልፏል።
እንዲሁም፣ በባለስልጣኑ ፈቃድ ባልተሰጣቸው ደላሎች እና አሻሻጮች አማካኝነት ወይም ከተፈቀደው የገበያ ሥርዓት ውጭ አክሲዮኖችን እንዳይገበያይ አሳስቧል።
በሔለን ተስፋዬ