በቅርቡ አዲስ አበባን ከጎበኘች በኋላ በከተማዋ ልማት በመደመም የኬያዋን ዋና ከተማ ናይሮቢ ከአዲስ አበባ ጋር ያነጻጸረችው ጋዜጠኛ ማርያን አንያንጎ ኬንያ ከኢትዮጵያ መማር ያለባት ብዙ ነገር እንዳለ ገልጻለች።
የኬንያው ጋዜጣ “ዘ-ስታንዳርድ” በአዲስ አበባ ከተማ በፍጥነት እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት እና በኢትዮጵያ በራስ የመመካት ልማት ሞዴል ላይ አድናቆቱን ገልጿል።
Firework with Thee Anyango በሚል አምድ ላይ እንዳሰፈረችው የኢትዮጵያን ልምድ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ምሳሌ አድርጋ አቅርባለች።
ዘስታንዳርድ ጋዜጣ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት ያሳየችው ስኬት የመጣው ከአይኤምኤፍ (IMF) ብድር ሳይሆን፣ በራሷ ግብር ከፋይ ዜጎች መዋጮ መሆኑን አስምሮበታል።
ይህ በራሱ ወጪና በራሱ ባለሙያዎች የመሥራት ልምድ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም የገነቡት ታላቁ የህዳሴ ግድብ (GERD) ውጤት መቀጠያ መሆኑን ጋዜጣው ገልጿል።
ጋዜጣው የኬንያ መሪዎች አሁን ላይ “ሀገራችንን በአምስት ዓመት ውስጥ እንደ ሲንጋፖር እናደርጋለን” ከሚል መፈከር ይልቅ፣ “እንደ ኢትዮጵያ ” የሚለውን የሀገር ውስጥ አቅምን የመጠቀም ሞዴል እንዲከተሉ ግልጽ የሆነ ምክር ለግሷል።
አዲስ አበባ አሁን ላይ በአረንጓዴ ዛፎች ያሸበረቀች፣ ጽዱ እና ለትራፊክ ፍሰት ምቹ የሆነች ተምሳሌታዊ ከተማ መሆኗ ተገልጿል።
ከተማዋ በጠንካራና ትጉ ሴት ከንቲባ እየተመራች መሆኗን የገለጸው ጋዜጣው፣ በውሃ ፋውንቴን፣ ከብሔራዊ መዝሙር ጋር በተጣመረ የብርሃን ትርኢት እና በሰፋፊ ፓርኮች ያሸበረቀች “አፍ የምታስከፍት መዲና” ሆናለች ሲል ዘግቧል።