ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኡራኤል ብራስ ፣ቦሌ መድኃኔዓለም ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን መገምገማቸዉን ገለጹ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኡራኤል ብራስ ፣ቦሌ መድኃኔዓለም ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን መገምገማቸዉን ገለጹ

AMN ሕዳር 30/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማለዳ ከኡራኤል ብራስ ፣ ቦሌ መድኃኔዓለም ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን ገምግመናል ብለዋል።

ይህ ኮሪደር በከተማችን በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ለማስፋት የተጀመረ ዘጠነኛው ኮሪደር ሲሆን፣ አጠቃላይ 11.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና በውስጡ በርካታ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎችን የያዘ ነው።የግንባታው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከኮሪደሩ በተጨማሪም ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የኖረ፣ ከሕዝብ ተወስዶ በግለሰቦች ያለአግባብ ተወሮ ለብዙ ብልሽት ተዳርጎ የኖረውን ታሪካዊውን የፒኮክ ወይም በጥንታዊ መጠሪያ ስሙ ማዕከላዊ ፓርክን ከወንዝ ዳርቻ ጋር አያይዘን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያለማነው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ሌላኛው የስበት ማዕከል፣ ድንቅና ውብ ስፍራ ሆኖ እየተገነባ ነው።

በተለይም የCOP 32 ጉባኤ በሚከናወንበት በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ አስቀድመዉ የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በዚህ አጋጣሚ የCOP 32 ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ፣ ይህ ጉባኤ በመዲናችን መዘጋጀቱ ከአገር መልካም ገፅታ ግንባታ በተጨማሪ፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ትስስር እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ወደ አገራችን በቀጣይነት ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚፈጥር ስለሆነ ከመቼውም የበለጠ ትኩረት ይሻል።

በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጉባኤው ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጦ እንድንጠቀም እና ለጉባኤው ስኬታማነትም ከወዲሁ ሁላችንም ዝግጅት እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review