የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ እና አምራቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በቅንጅት ለመፍታት የሚያስችል የውይይት መድረክ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ አምራቾች ጋር አካሂዷል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የመብራት መቆራረጥ፣ በቂ የውሃ አቅርቦት አለመኖር እና የመንገድ መሰረተ ልማት አለመሟላት በምርታማነታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮብናል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የተለያዩ ተቋማት ሀላፊዎችም ለተነሱት ጥያቄዎች የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰጥተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጂኖች ማስተባበሪያ ቢሮ አቶ ሸዋይርገድ ኃይሌ መብራትን በተመለከተ በአምራቾች በኩል የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት በአጭርና በረጅም ጊዜ ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ በበኩላቸው የውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ከመንገድ ጋር በተያያዘ በአምራቾች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በባለስልጣኑ እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚመለሱ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው በአምራቶች በኩል የሚነሱ የመስሪያ ቦታ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት መድቦ ትላልቅ የኢንዱስትሪ ክላስተር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ አምራቾችም ወደ እዚህ ክላስተር እየገቡ የሚሰሩበት አሰራር መዘርጋቱንም አቶ ጃንጥራር ገልጸዋል፡፡
የአምራቾችን ችግሮች ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ጃንጥራር ችግሮችን በሂደት ለመፍታትም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅድሚያ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን