ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራሟን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ስታንዳርድና መመሪያዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደምትተገብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኑክሌር ኢነርጂ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሜካኤል ቹዳኮቭ (ዶ/ር) ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጋር ትብብርን በሚያጠናክሩ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይልና ቴክኖሎጂን ለንጹህ ኢነርጂ፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለምርምር ልህቀት የመጠቀም ጽኑ መሻት እንዳላትም አመልክተዋል።
ለዚህም ሀገራዊ የኑክሌር ኃይል ፕሮግራምን በቅርቡ መጀመሯንና የኑክሌር ኃይል ኮሚሽንን በማቋቋምም በይፋ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራሟን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ስታንዳርድና መመሪያዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደምትተገብርም አረጋገጠዋል።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢትዮጵያ ከኑክሌር ኃይል ስትራቴጂካዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ እውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹላቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።