ከእናት ጡት ወተት እና ከላም ወተት ለሕጻናት ተመራጭ የቱ ነው?‎‎

AMN- ታህሳስ 1/2018 ዓ.ም

‎‎የላም ወተት እና የእናት ጡት ወተት ከፍተኛ የሆነ የፕሮቲን ልዩነት አላቸው።

‎‎የእናት ጡት ወተት ሕጻናት በተወለዱ በመጀመርያዎቹ ቀናት ፣ወራት እና ዓመት ሲሞላቸው የፕሮቲን ይዘቱን አንደ ሕጻናት እድገት እና እንደሚያስፈልጋቸው መጠን በተፈጥሮ ዝግጅቶች እያስተካከለ የሚሄድ ነው።

‎‎ለሕጻናት የላም ወተት ሲሰጥ ሁሌ አንድ አይነት ስለሚሆን የተመጣጠነ ንጥረ ነገር ማግኘት እንደማይቻል የሕጻናት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሰላም ብስራት ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።‎‎

በመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የሕጻናት የአዕምሮ እድገት ሰማንያ በመቶ የሚያድግበት ወቅት ስለሆነ ጥሩ የሆነ የመቀበል አቅም ያለው አዕምሮ አንዲኖራቸው ከእናት ጡት ወተት የሚያገኘው የስብ አይነት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

‎‎በዚህ ወቅት የላም ወተት የሚጠጡ ህፃናት ይህን እንደማያገኙም ገልጸዋል።‎‎የላም ወተት ከፍተኛ የሆነ የፕሮቲን መጠን እንዳለው እና በሕጻናት ላይ የአንጀት ቁስለት እና በዓይን የማይታይ የደም መድማት ያመጣል።

‎‎ይህ ደግሞ ከአይረን እጥረት የሚመጣ ከመሆኑ ባሻገር የደም ማነስም ያስከትላል ብለዋል።‎‎

ልጅ ከተወለደ በኋላ በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ ከእናት ጡት ወተት ጋር ቢገናኝ መልካም እንደሚሆን መክረዋል።‎‎የላም ወተት በተለይ ህጻናት በተወለዱ የመጀመርያው አንድ ዓመት ባይሰጥ መልካም መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ሰላም፣ እስከ ስድስት ወር ያለው ጊዜ ካለምንም ተጨማሪ ምግብ ጡት በማጥባት ብቻ ልጅ ማሳደግ እንደሚገባ እና ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ያለውን የእድገት ጊዜ ከተጨማሪ ምግብ ጎን ለጎን የእናት ጡት ወተት መሰጠት እንዳለበት ይመክራሉ።

‎‎የመጀመሪያው ሶስት ቀናት እናት ጡት ወተት ምርት በደንብ እንደሚጨምር እና ለሊትንም ጨምሮ በሁለት እና በሶስት ሰዓታት ልዩነት ማጥባት እንደሚያስፈልግ፤ ይህ ከሆነ የሚያጠቡት የወተት መጠን እንደማይቀንስ አብራርተዋል።‎‎

አጥቢ እናቶች በበቂ መጠን ምግብ በሰዓት መመገብ፣ ፈሳሽ መውሰድ እንደሚገባቸው ያስረዱት ዶ/ር ሰላም የእናት ጡትን በሌላ ነገር ለመተካት መሞከር የጡት ወተት መጠኑን እንደሚቀንሰው ነግረውናል።‎‎

ጡት ማጥባት እናትየውንም ሆነ ሕጻኑን ከተለያዩ በሽታዎች እንደሚጠብቃቸው በተለይ እናትየውን ከስኳር እና ከካንሰር ህመም እንደሚታደግ አብራርተዋል።‎‎

የላም ወተት ሕጻኑ በተወለደ የመጀመርያው አንድ ዓመት ውስጥ ባይሰጥ የሚመክሩት የሕጻናት ሀኪሟ፣ ሕጻናት በመጀመርያው ስድስት ወር ያለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናት ጡት ብቻ መጥባት አለባቸው ብለዋል።‎‎

 ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ የእናት ጡት ወተት እና ተጨማሪ ምግብ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎‎ይህ ደግሞ እናትየው ከአንደኛው አይነት የስኳር ህመም፣ ከካንሰር እንደሚከላከል እና ለእናትም ሆነ ለልጅ በርካታ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።‎‎

ይህ ማለት የላም ወተት ፍጹም አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ እና ሕጻኑ ከተወለደ ከአንድ ዓመት በኋላ መጠኑ ሳይበዛ ቢሰጥ መልካም እንደሚሆን እና መጠኑ ከበዛ የሕጻኑን የምግብ ፍላጎት እንደሚገድብ እና ይህ ደግሞ ማግኘት የሚገባቸውን ንጥረ ነገር እንዳያገኙ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

‎‎በተለያዩ ምክያቶች እናት ባትኖር ወይም ማጥባት ባትችል እንኳ፣ ለሕጻናቱ የሚሰጠው የወተት መጠን መመጠን እንዳለበት እና በውሃ ቀጥኖ መጠኑ ከግማሽ ሊትር በታች መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።‎‎የእናት ጡት ወተት በብዙ ምክንያት ለእናትየውም ሆነ ለሕጻኑ በጣም ብዙ ጥቅም እንዳለው ዶ/ር ሰላም ተናግረዋል።

‎‎የላም ወተት ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ የእናት ጡት ወተት ማጣት ለሕጻናት ከፍተኛ ጉዳት ስላለው ወላጆች ለልጆቻቸው የእናት ጡት ወተት የመጀመርያ ምርጫቸው እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

‎‎በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review