የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ

You are currently viewing የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ

AMN ታህሳስ 1/2018

የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።

በሕንድ፣ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ ጉባኤ ተካሂዷል።

በዚህ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ያቀረበችው የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በሰው ልጅ የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ዝርዝር ስር ተመዝግቧል።

“ጊፋታ” በወላይታ ማኅበረሰብ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የሕዝቡ የማንነት መገለጫ የሆነ የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡

ጊፋታ እድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ ማኅበራዊ ደረጃ ሳይለይ ለሁሉም ሠላም እና ማኅበራዊ ትሥሥር አስተዋጽኦ በማድረግ በዩኔስኮ የተለዩትን ዘርፎች ያካተተ ሁሉን አቀፍ ተግባራትን በማበረታታት የሚከበር በዓል መሆኑ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አስችሎታል።

በሀገራችን 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በተከበረ ማግስት የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል፣ “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ አጋጣሚውን ታሪካዊ ያደርገዋል።

በዚህ ጉባዔም ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ቱሪዝም ሚንስትር ሠላማዊት ካሳ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ንግግር አስደምጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review