አውስትራሊያ ታዳጊ ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግደውን ህግ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረች

You are currently viewing አውስትራሊያ ታዳጊ ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግደውን ህግ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረች

AMN- ታህሳስ 1/2018 ዓ.ም

አውስትራሊያ በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን ታዳጊ ወጣቶች ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንዳይጠቀሙ የሚያግደውን ህግ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡

ሀገሪቱ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን የከለከለች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡

ይህም በብዙ ወላጆች እና የልጆች መብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ በንግግር ነፃነት ተሟጋቾች እና በታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዘንድ ትችት ተሰንዝሮበታል።

በሀገሪቱ አቆጣጠር ከማክሰኞ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ቲክቶክን፣ አልፋቤትን፣ ዩቱብ፣ እና ፌስቡክን ጨምሮ 10 ትልልቅ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ኩባንያዎች ህፃናትን እንዲያግዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ኩባንያዎቹ ትዕዛዙን የማይተገብሩ ከሆነ አዲስ በወጣው ህግ መሠረት እስከ 33 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ቅጣት እንደሚቀጡ ተገልጿል።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ፣ ዕለቱን ለቤተሰቦች “የኩራት ቀን” ሲሉ ጠርተውታል፡፡

“ውሳኔው ትልቅ ለውጥ ያመጣል” ያሉት አልባኔዝ፣ ይህ በሀገራቸው ከመጡ ትላልቅ ማህበራዊ እና ባህላዊ ለውጦች አንዱ መሆኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

እርምጃው በዓለም ዙሪያም የሚቀጥል ጥልቅ መሻሻል ነው በማለትም ገልጸውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒዝ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ልጆች በዚህ ወር መገባደጃ ከሚጀምረው የአውስትራሊያ የክረምት ትምህርት ዕረፍት በፊት “አዲስ ስፖርት እንዲጀምሩ ወይም መደርደሪያ ላይ የቆዩ መጽሐፍትን እንዲያነቡ ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review