ሪያል ማድሪድ ከማንችስተር ሲቲ ፦ ዣቪ አሎንሶ እና ፔፕ ጋርዲዮላን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ

You are currently viewing ሪያል ማድሪድ ከማንችስተር ሲቲ ፦ ዣቪ አሎንሶ እና ፔፕ ጋርዲዮላን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ

AMN ታህሣሥ 01 ቀን 2018 ዓ.ም

ሪያል ማድሪድ ከ ማንችስተር ሲቲ በቅርብ ዓመታት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ድምቀት ሆኗል።

ሁለቱ ክለቦች ለዘመናት የሚታወሱ ድንቅ ፉክክሮችን አድርገዋል።

የዛሬውም ጨዋታ ላቅ ያለ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የጨዋታው ውጤት በተለይ ለሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ በእጅጉ ያስፈልጋል።

የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ ከአምስት የላሊጋ ጨዋታ ቡድኑ ያሸነፈው አንዱን ብቻ ነው።

በተለይ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ በሴልታ ቪጎ መሸነፉ የክለቡን ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ አስቆጥቷል።

ከባርሰሎና በአራት ነጥብ የራቀው ቡድናቸው ውጤቱን ካላሻሻለ አሰልጣኙ በቦታው እንደማይቆይ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ተብሏል።

የዛሬ ምሽቱ ጨዋታ ውጤትም የአሰልጣኙን ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅም እንዳለው ከስፔን የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ መሻሻል ያሳየው ማንችስተር ሲቲ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውጤቱ የሚያስመካ አይደለም።

ከአምስት ጨዋታ 10 ነጥብ የያዘው ሲቲ ቀጥታ ወደ ጥሎማለፍ ከሚገቡ ስምንት ክለቦች አንዱ ለመሆን ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይፈልጋል።

ሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር ሲቲ የዛሬ ግንኙነታቸው ለ15ኛ ጊዜ ነው።

የእንግሊዙ ክለብ አምስቱን በማሸነፍ የቻምፒየንስ ሊጉ ንጉሱ ላይ የበላይነት አለው።

የ15 ጊዜ የውድድሩ ባለድል ማድሪድ ሲቲን አራት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።

ዣቪ አሎንሶ የባየርን ሙኒክ ተጫዋች እያለ በፔፕ ጋርዲዮላ ሰልጥኗል።

አሎንሶ ወደ አሰልጣኝነቱ ከመጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ አለቃውን በተቃራኒ ይገጥማል።

በዛሬው ጨዋታ በማድሪድ በኩል አማካዩ ኤድዋርዶ ካማቪንጋ ከስብስቡ ውጪ ሆኗል።

አሌክሳንደር አርኖልድ ፣ ዲን ሃውሰን ፣ ኤደር ሚሊታኦ ሌሎች ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።

ግብ በማስቆጠሩ ትልቅ ሃላፊነት የተሸከመው ኪሊያን እምባፔ መግባቱ አጠራጣሪ ሆኗል።

ፈረንሳዊው አጥቂ በሴልታቪጎ በተሸነፉበት ጨዋታ የጉልበት ጉዳት እንደገጠመው ማርካ ዘግቧል።

ተጫዋቹ በሁሉም ውድድር 25 ግብ ማስቆጠር የቻለ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ነው።

ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት በዋና ዳኛው ክሌሞን ተርፓን ፊሽካ ይጀመራል።

በሌሎች የዛሬ ምሽት ጨዋታዎች አርሰናል የቤልጂየሙን ክለብ ብሩዥን ከሜዳው ውጪ ይገጥማል።

በመድፈኞቹ በኩል ዴክለን ራይስ በህመም ፣ ሊአንድሮ ትሮሳርድ ደግሞ በጉዳት ምክንያት በጫዋታው አይሳተፉም።

አትሌቲክ ቢልባኦ ከፓሪሰን ዠርማ ፣ ባየር ሊቨርኩሰን ከኒውካስትል ዩናይትድ ፣ ቤኔፊካ ከናፖሊ ፣ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ከቦዶ እንዲሁም ጁቬንቱስ ከፓፎስ በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት የሚጀምሩ ጨዋታዎች ናቸው።

ካራባግ ከአያክስ እና ቪያሪያል ከኮፐንሃገን ቀደም ብለው ምሽት 2:45 ይጀምራሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review