በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት የተከናወነው 20ኛው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በላቀ ስኬት መጠናቀቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ::
የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔላዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ የተከናውነው 20ኛው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የታለመለትን ዓላማ አሳክቶ፣ በላቀ ደረጃ፣ በሰላም መጠናቀቁ አስታወቀዋል።
በዓሉ በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በፌዴራል ተቋማት ከኅዳር 1 ቀን 2018 ዓ. ም ጀምሮ በልዩ ልዩ ሁነቶች እንዲከበር የበዓሉ አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት የፌዴራል ተቋማት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለበዓሉ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በደመቀ ሁኔታ ማክበር መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
አቶ አገኘሁ አያይዘውም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እንዲከበር የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲወሰን ዓላማው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እሴቶቻቸውን፣ ልምዶቻቸውንና ባህሎቻቸውን በመለዋወጥ ብዝኀነታቸውን መሠረት አድርገው ኅብረብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም፣ ለፈጣን ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲነሳሱ ማድረግ እና በሕገመንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤ በማጎልበት አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማስቻል መሆኑን አስታውሰዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከበሩ በዓላት ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲያጠናክሩ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያፀኑ፣ አስተናጋጅ ክልሎች ከፍተኛ የሆነ የገጽታ ግንባታና የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠሩ፣ በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያጎለብቱ እና አገራችን የምትከተለው የፌዴራል ሥርዐት በጥንካሬና በሰከነ መንገድ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡
ለዚህም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት የተከበረው በዓል ቀዳሚ አብነት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዓሉ በአማረ ሁኔታ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ለአስተባባሪው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራሮችና ፈፃሚዎች፣ ለአስተናጋጁ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮችና ባለሙያዎች ከፍተኛ ምስገናቸውን ገልጸው በተለይ ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ላሰየው ልባዊ የእንግዳ ተቀባይነት፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት መንፈስ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል::
ከሚዲያ ጉብኝት ጀምሮ በዚህ በዓል ላይ በመታዳም አጠቃላይ ሁነቶችን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደራሽ ላደረጉ ለሁሉም የሚዲያ አካላት የላቀ ምስጋና ማቅረብ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የተለያዩ የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ አደረጃጀቶች ከፍተኛ አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
አቶ አገኘሁ በዓሉ የወል ትርካቶቻችንን በሚያሳድግ፣ ኅብረብሔራዊ አንድነታችንን በሚያጎለብት፣ አገራዊ ገጽታችንን በሚገንባ፣ ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን መረጋገጥ በአንድነት እንድንቆም በሚያስችል፣ ለአገረ መንግሥት ግንባታችን ትልቅ አበርከቶ ባለውና የአስተናጋጁን ክልል ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት በአረጋገጠ በዚህ ደረጃ ከፍ ብሎ መከበሩን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጉ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ምስጋና ማቅረባቸዉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡
ቀጣዩ 21ኛው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ታሪካዊቷ ጅማ ከተማ ለማዘጋጃት እንደተመረጠች ይታወሳል።