የአየር ንብረት ለውጥ የአእምሮ እድገትን ሊያዘገይ እንደሚችል ባለሙያዎች አሳሰቡ
የአየር ንብረት ለውጥ በልጆች አእምሮአዊ እድገት ላይ ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል ሰሞኑን ይፋ የተደረገ አዲስ ጥናት አመላክቷል፡፡
ከተለመደው የሙቀት መጠን ከ86 ዲግሪ ፋራናይት በላይ ለሆነ ሙቀት የሚጋለጡ ልጆች የሥነ ጽሑፍና የሂሳብ ችሎታቸው አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪዎች መግለፃቸውን ዩፒአይ አስነብቧል፡፡
በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የተግባር ሳይኮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ጆርጅ ኩዋርትስ የተባሉ ተመራማሪ እንደገለጹት፣ በህፃናት እድገት ላይ የሚከሰተው ቅድመ ውስንነት በቀጣይ ህይወታቸው ማለትም በትምህርት፣ በአካል እና በአእምሮ ጤና እንዲሁም አጠቃላይ ደህንነታቸው ላይ መሰረት እንደሚጥል ተናግረዋል፡፡
የጥናቱ ግኝትም ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ባለሙያዎች በሞቃታማ አካባቢ የሚገኙ ህጻናትን እድገት ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያስችላል ብለዋል።
በጥናቱም በጋምቢያ፣ በማዳጋስካር፣ በማላዊ እና በሴራሊዮን የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም በጆርጂያ፣ በጥቁር ባህር አካባቢ በሚገኙ ብሔረሰቦችና እና በፍልስጤም የሚገኙ ከ19 ሺህ 600 በላይ የ3 እና የ4 ዓመት ህጻናት መካተታቸውን በዘገባው ተገልጿል፡፡
የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየውም በአማካይ ከፍተኛው ከ86 ዲግሪ ፋራናይት በላይ ለሆነ ሙቀት የተጋለጡ ህጻናት፣ ከ79 ዲግሪ ፋራናይት ባነሰ የሙቀት መጠን ጋር ሲነፃፀሩ ለንባብ፣ ለፅሁፍ እና ለሒሳብ መሰረታዊ እድገት የማሟላት እድላቸው ከ 5 እስከ 7 በመቶ እንደቀነሰ ማሳየቱን ዘገባው አስነብቧል፡፡
በአስማረ መኮንን