የአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት በከተማዋ በሰው ሰራሽና በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለመከላከል እና የኑሮ ጫናን ለማቃለል እየሠራ ይገኛል።
ድርጅቱ ይህንን ለማድረግ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲሁም የምግብ ዘይትን ከውጭ በማስገባት በዝቅተኛ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡና ለተቋማት እያቀረበ ይገኛል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ መስፍን አሰፋ እንደተናገሩት፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 5.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ በማስገባት ለኅብረተሰቡ ተሰራጭቷል።
ድርጅቱ ባለአምስት ሊትር ፈሳሽ ዘይትን ከመደበኛው ዋጋ አንጻር ቅናሽ በማድረግ በአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ለተቋማትና ለማኅበራት እያቀረበ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ 15 ቀናት ውስጥም ተጨማሪ ዘይት በማስገባት የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ከድርጅቱ የዘይት ምርት ሲገዙ ያገኘናቸው ሸማቾችም በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸመቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት በከተማዋ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
በሔለን ጀንበሬ