ኢትዮጵያ የብዝሃነት አምባ ናት፡፡ ብዝሃነት ውበትና ድምቀቷ ነው፡፡ እነዚህ ብዝሃ-ማንነቶች የሰሯት አገር ብትሆንም፤ ብዝሃነቱ ተገቢውን እውቅና አግኝቶ፣ በእኩልነት፣ በዴሞክራሲና በሰላም መኖር የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት አልነበረም።
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸው ታውቆ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ተከብሮ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ መኖር የሚችሉበት ስርዓት ይፈጠር ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ትግል ሲካሄድ እንደነበር በፌዴራሊዝምና በመንግስታት ግንኙነት ዙሪያ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉትና በአሁኑ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ በላይ ወዲሻ ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በዋናነት ሶስት ናቸው፤ የብሔር፣ የመሬት እና የዴሞክራሲ፡፡ የንጉሱን ስርዓት በተካው የደርግ መንግስት የመሬት ላራሹ ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ነበር የቀጠሉት፡፡ በዚህ ምክንያት ለአስራ ሰባት ዓመታት ሀገሪቱ በዕርስ በዕርስ ጦርነትና ውድመት እንድትቆይ አድርጓል፡፡ በ1983 ዓ.ም የመጣውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ብዝሃነትን ለማስተናገድ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓትን መከተል እንደጀመረች አቶ በላይ ይገልፃሉ፡፡
“ከ1983 ዓ.ም በፊት የነበረው አስተዳደር ማዕከላዊና ብዝሃ ማንነትን የማያስተናግድ በመሆኑ ምክንያት ግጭትና ጦርነት ፈጥሮ፣ የሀገር አንድነትና ቀጣይነት ስጋት ውስጥ ወድቆ ነበር” የሚሉት በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ የፌዴራሊዝምና ህገ መንግስት መምህር ሱልጣን ቃሲም፤ የፌዴራል ስርዓትን ሀገራት እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ያደርጉታል፡፡ በኢትዮጵያ መተግበር ያስፈለገበት ምክንያትም ብዝሃነትን በአግባቡ ለማስተናገድና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመንግስት አስተዳደር ስርዓት ውስጥ ፍትሀዊ ውክልና ማግኘት እንዲችሉ ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓትን መከተል ከጀመረች ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በስርዓቱ መተግበር ምን ትሩፋት ተገኘ? ክፍተቶችስ ምንድን ነበሩ? ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያለው ሀገር ለመፍጠር ምን መሰራት አለበት? የሚለውን እንደሚከተለው ዳስሰነዋል፡፡
የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ትሩፋት
ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓትን መከተል ከጀመረች በኋላ በተለያየ መልኩ የሚገለፁ መልካም ውጤቶች መገኘታቸውን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። የፌዴራሊዝም ምሁሩ ሱልጣን እንደሚሉት፣ “ይህ ስርዓት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸው እንዲታወቅና እንዲከበር ያደረገ፣ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን… የሚያዳብሩበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ፣ ሀገሪቱን ሊበታትን የሚችል ግጭትና ጦርነት ጋብ እንዲል አድርጓል።”
ለረጅም ጊዜ ‘መብታችን አልተከበረም፤ ማንነታችን እውቅና አላገኘም’ በሚል የጠመንጃ ትግል በማድረግ እስከ መገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደነበሩ የሚያነሱት የፌዴራሊዝም ምሁሩ ሱልጣን፣ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ ምክንያት እነዚህ ህዝቦች በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ መኖር እንደሚችሉ ማመን የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ “የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ሀገርን ሊበትን ይችል ለነበረ የፖለቲካ ጥያቄ መልስ በመስጠት ለሀገር አንድነትና ቀጣይነት አስተዋፅኦ አድርጓል” ይላሉ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ በላይ፣ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪካቸውን የመጠቀም፣ የማሳወቅና የማሳደግ መብት አግኝተዋል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና ያገኙ 76 ብሔሮችና ብሔረሰቦች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ህዝቦች ከዓመታት በፊት እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም ነበር፡፡ በ“ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን” እና በተለያዩ መድረኮች አንድ ላይ ተሰባስበው ባህል፣ ታሪክና ወጋቸውን የሚያሳዩበት፣ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት፣ ባህላቸውን የሚለዋወጡበት፤ በመካከላቸው መከባበር፣ ትስስርና አንድነት የሚጠናከርበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በአካል ብቻ ሳይሆን በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ እሴቶቻቸውን የሚያሳዩበትና የሚሸጡበት ዕድል ማግኘት ችለዋል። ይህም ኢትዮጵያውያን፣ ‘ኢትዮጵያ ብዝሃነት ያለባት ሀገር’ መሆኗን እንዲያውቁ፣ መከባበርና አንድነት እንዲጠናከር ዕድል መፍጠሩ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ሌላኛው ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው ያስገኘው ትሩፋት ከኢኮኖሚ ጋር እንደሚያያዝ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ሱልጣን ያነሳሉ፡፡ “ስርዓቱ በተበታተነ ትናንሽ ሀገር ከመኖር ይልቅ በአንድ ትልቅ ሀገር የጋራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብን መገንባት ዓላማ አድርጎ የተነሳ በመሆኑ ትልቅ ገበያ መፍጠር አስችሏል፡፡ ክልሎች ከክልሎች፣ እንደሀገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰፊ የሆነ ገበያ ማካሄድ የሚቻልበትን መሰረት ጥሏል፡፡” ሰፊ ገበያና ሰፊ ሀገርን ማስቀጠል መቻሉ ደግሞ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ያብራራሉ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ በላይ እንዲሁ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ልማትን በማፋጠን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እያገዘ እንደሚገኝ ያነሳሉ፡፡ ለምሳሌ ብዙዎቹ በክልል የሚገኙ ስታዲየሞች፣ አዳራሾች፣ ሆቴሎች፣ የመንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና ሌሎች የከተማ ልማቶች የተሰሩት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ ነው። ለምሳሌ፡- ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓሉ በሚከበርባት ሆሳዕና ከተማ፣ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ አንድ ስታዲዬም ገንብቶ መጨረስ የተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ያጋጠሙ ክፍተቶች፣ ማስተካከያዎችና ቀጣይ መፍትሔዎች
ከፌዴራሊዝም ስርዓቱ አተገባበር ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉ ሲነገር ይደመጣል፡፡ አንዳንዶች ስርዓቱን ከአወቃቀሩ ጀምሮ ‘ብሔርና ቋንቋ ማዕከል ያደረገ ነው’ የሚል ትችት ያቀርባሉ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ይህንን ሀሳብ አይቀበሉትም፡፡ “የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ህብረ ብሔራዊ አወቃቀርን የተከተለ ነው፡፡ አንዳንዶች ‘የጎሳ፣ የብሔር ነው’ ይላሉ፡፡ ነገር ግን ብሔርን ብቻ መሰረት አድርጎ የተዋቀረ አይደለም፤ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 39፣ 46 እና 47 ላይ ብናይ ክልሎች የሚዋቀሩት ምክንያት ተመሳሳይ የሆነ ሥነ- ልቦና፣ መልክአምድራዊ አቀማመጥ፣ ኩታገጠምነት፣ ቋንቋና ባህል፣ በአንድ ክልል የመደራጀት ፈቃደኝነት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው፡፡” በማለት ያብራራሉ፡፡
አተገባበሩ ላይ ግን ክፍተቶች እንደነበሩት አቶ በላይ ያነሳሉ፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በአብዛኛው በነጠላ ትርክት ወይም አንድ ብሔር ላይ የታጠሩ ስራዎች ጎልተው ይሰሩ ነበር። በዚህ ምክንያት የብሔር አክራሪነትና ዋልታ ረገጥነት በመስፋፋቱ ግጭትና መጠራጠር ተፈጥሯል፡፡ በአንድ ክልል ውስጥ ‘አንተ የእኔ ነህ’፤ ‘አንተ/ቺ የእኔ አይደለህም/ሽም’ የሚል ስሜት፤ አንዱ ሌላውን የማግለል አዝማሚያ ታይቷል። ይህ ዓይነቱ አካሄድም ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው በትግበራው ያጋጠመ ክፍተት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ሌላው በህብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ሁሉም ክልሎች እኩል እንደሆኑ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ግማሾቹ በሀገራዊ ጉዳይ ባለቤት በመሆን የመወሰን መብት ሲኖራቸው፣ ሌሎች (እንደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ሐረር…ያሉ ክልሎች) በድርጅት ስም ‘አጋር’ ተብለው የመወሰን ስልጣን አልነበራቸውም፡፡ ተግባሩ በፓርቲ አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን በመንግስት መዋቅር ጭምር ይታይ ነበር። ይህም ስርዓቱን ጎዶሎ አድርጎት ነበር የሚሉት አቶ በላይ፣ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ይህ የታረመበት፤ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት ተግባራዊ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የፌዴራሊዝም ምሁሩ አቶ ሱልጣን በበኩላቸው፤ በተለይ በኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን ህገ መንግስቱ ለይስሙላ እንጂ ሀገር ይመራ የነበረው በዋናነት በፓርቲ ፕሮግራም እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ህገ መንግስታዊ ማዕቀፎችና መርሆች ተጥሰው፣ ሀገሪቱ የፌዴረዳሊዝም ስርዓትን የምትከተል ቢሆንም ውሳኔዎች በማዕከላዊ ፓርቲ አደረጃጀት አማካኝነት ነበር የሚሰጡት፡፡
የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ክልሎች ያላቸውን መሬት፣ ማዕድናትና የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች በባለቤትነት የመጠቀም መብትን ያጎናፀፈ ቢሆንም የነበረው አስተዳደር ሀብቶች በሚገኙበት አካባቢ ያለውን ማህበረሰብ ትኩረት ባለመስጠቱ ብዝበዛዎች ነበሩ፡፡ ውሎ አድሮም በነበረው አስተዳደር ላይ ተቃውሞዎች እንዲነሱ በማድረግ በመጨረሻ የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ አንድ ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ሱልጣን ያስረዳሉ።
ሀገራዊ ማንነት ግንባታ ላይ ብዙ አለመሰራቱ የስርዓቱ ሌላኛው ጉድለት ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ እንደገለፁት፣ ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ከሀገራዊ ይልቅ የብሔር ማንነት ጎልቶ የወጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ “የተለያየ ብሔር ሊኖረን፣ የተለያየ ቋንቋ ልንናገር እንችላለን፤ ስንሰባሰብ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነት ይኖረናል፡፡ በዚህ ረገድ የሚያሰባስብና የሚያጋምድ ትልቅ ሀገር እንድንፈጥር የሚያስችለን ትርክት ያስፈልጋል፡፡ በመሰረታዊነት ኢትዮጵያዊ ማንነት ጎልቶ መውጣት እንዳለበት” አቶ በላይ ያነሳሉ፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢህአዴግ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) አባልና አጋር የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልሎች ነበራቸው፡፡ በየራሳቸው ፓርቲ ተወያይተው በራሳቸው ክልል የሚወስኑበት፣ እንደሀገርም የሚነጋገሩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ሀገር እየመራ ያለው ፓርቲ ወጥ የሆነና ለሁሉም አባላት እኩል እድል የሚሰጥ በመሆኑ አንድ አጀንዳ ሲቀረፅ በሁሉም አካባቢ ሀገራዊ ይሆናል፡፡ ህብረ ብሔራዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ እንደሀገር የሚወሰኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ ውይይት የሚደረግባቸው አግባብ ተፈጥሯል፡፡ ሀገራዊ ማንነትንና ክልላዊ (ብሔረሰባዊ ማንነትን) ሚዛናዊ ለማድረግ የፓርቲ አደረጃጀቱ እድል ሰጥቷል ይላሉ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ በላይ፡፡
በፌዴራል እና ክልል መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት የሚመራበት የመንግስታት ግንኙነት አለመኖርም ሌላው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ክፍተት ነበር፡፡ የመንግስታት ግንኙነት አዋጅ ሲረቀቅ የኮሚቴ አባል በመሆን ከሰባት ዓመታት በላይ መስራታቸውንና ውድቅ ሲደረግ መቆየቱን የሚያነሱት አቶ በላይ፣ ስራዎች የሚሰሩት በፓርቲ መስመር ብቻ በመሆኑ ህጉ እንዲወጣ አይፈለግም ነበር፡፡ ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ በኋላ ግን ፀድቆ ወደ ተግባር መግባቱን ያስረዳሉ፡፡
“የመንግስታት ግንኙነት የሚመራበት ህግ ሳይኖር አንድ የፌዴራል ስርዓት ጠንካራ ሊሆን አይችልም” የሚሉት አቶ በላይ፣ የመንግስታት ግንኙነት በክልልና ፌዴራል መንግስት መካከል ያሉ ጉዳዮች በውይይት፣ ንግግር፣ በድርድር፣ ሰጥቶ መቀበል ችግሮች የሚፈቱበት፣ ፖሊሲ የሚተነተንበት፣ እንደሀገርም ሀገራዊ አጀንዳዎች የጋራ የሚደረግበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህም ለፌዴራሊዝም ስርዓቱ መጠናከር የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ቀጣይ ስራዎች
እንደ አቶ በላይ ገለጻ፣ አንድ ስርዓት በአንድ ጀምበር ሳይሆን በትውልድ ቅብብሎሽ ነው የሚገነባው፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት በተተገበረባቸው ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ተስፋዎች እና ሊሻገራቸው የሚገቡ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በፌዴራሊዝም ስርዓቱ አንዱና ትልቁ ተግዳሮት ነጠላ ትርክት፣ ብሔራዊ ማንነትና ነጠላ ማንነት ወይም ሀገራዊ ማንነት እና ብሔረሰባዊ ማንነትን ሚዛናዊ አድርጎ አለመሄዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡
ሌላው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ጉድለት የዴሞክራሲ እጦት ነው፡፡ የዴሞክራሲና ፖለቲካ ባህላችን ደካማ ከመሆኑ የተነሳ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ ትግበራ ላይ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ የፌዴራል ስርዓትና ዴሞክራሲ የሚነጣጠሉ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ከዚህ አኳያ በንግግር፣ ውይይትና ድርድር፣ በሰለጠነ መንገድ የውስጥ ችግርን መፍታት፣ የሀገር ጥቅምን ማስቀደም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራሊዝም ምሁሩ ቃሲም በበኩላቸው፣ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ በተሟላ መልኩ እንዲተገበር መንግስት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ማህበረሰቡ ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ችግሮችን ህገ መንግስታዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ላይ መስራት ይገባል፡፡ መገናኛ ብዙሃን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብቶች፣ ሀገራዊ ትርክቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። የመንግስት አካላትም ለህገ መንግስት ታማኝ በመሆን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው አካላት ከጠብመንጃ ይልቅ ሰላማዊ መፍትሔን በመምረጥ ቢሰሩ ዘላቂነት ያለው ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
.ሀገራዊ እና ብሔረሰባዊ ማንነቶችን ሚዛናዊ አድርጎ ለመሄድ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተጠቁሟል
በስንታየሁ ምትኩ