አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰራው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ በማድረግ አበረታች ውጤት መገኘቱን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።
በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ”ኩራት በሀገር ምርት!” በሚል መሪ ሀሳብ የ2018 4ኛው ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት አቶ ጃንጥራር አባይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል በትብብር መስራትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎች ችግር ሆነው የሚነሱ ጥያቄዎችን አስተዳደሩ ለመፍታት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሸቱ ለማ በበኩላቸው በክፍለ ከተማዋ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ወደ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለማሸጋገር የተለያዩ ተግባራቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በማድነቅ ይህንንም እድል በመጠቀም ምርትና ምርታማነታቸው እየጨመረና ምርቶቻቸውንም ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታዎችን እንደፈጠረላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ተናግረዋል።
ከጥቃቅንና አነስተኛ ተነስተው ወደ አምራች ኢንዱስትሪ በመሸጋገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየተፈጠረ መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል።
በመሀመድኑር ዓሊ