የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ ድርጅት በቅርቡ ባደረገው መጠነ-ሰፊ ሪፎርም ታሪካዊ የአገልግሎት እና የገቢ ዕድገት ማስመዝገቡን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አካሉ አሰፋ አስታወቁ። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በአደረጃጀት፣ በአሠራር፣ በቴክኖሎጂ እና በሠራተኞች ሥነ-ምግባር ላይ የነበረበትን ከባድ ችግር በመፍታት በአገልግሎት ዘርፍ ግንባር ቀደም ተቋም ለመሆን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጠው ድርጅቱ ከከተማዋ ዕድገትና የሕዝብ ፍላጎት ጋር መራመድ ባለመቻሉ ሲተች ቆይቷል። እንደ አቶ አካሉ ገለጻ፣ ድርጅቱ ከለውጡ በፊት ተቋሙን ለማስቀጠል ወደማይቻልበት ደረጃ ደርሶ ነበር። ይህ የከፋ ሁኔታ በተለይ በተጠቃሚዎች ዘንድ የሥነ-ምግባር ጉድለቶች እና የአገልግሎት ቅሬታዎች እንዲስተናገዱ አድርጓል።
የከተማው መንግስት ተቋማት የሕዝብ አገልጋይነትን እንዲላበሱ ለማድረግ በጀመረው የሪፎርም ስራ ውስጥ ያለፈው አውቶቡስ ድርጅት በአደረጃጀት፣ በአሠራር እና በቴክኖሎጂ ላይ የነበሩበትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ በመፍታት በአሁኑ ጊዜ በአንድ ቀን ከእጥፍ በላይ ቁጥሩን በማሳደግ ከ1.3 ሚሊዮን ለሚበልጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።

ኤ ኤም ኤን 24/7 በአገልግሎት መስጫ ፌርማታዎች ባደረገው ቅኝት በሰዓታቸው አገልግሎት ያለመስጠት፣ በሻይ ሰዓት ሰበብ የመዘግየት፥ ተገልጋይን የማመናጨቅ፣ የምልልስ ሰዓት ላይ መንጠባጠብ መኖሩን ለዋና ሥራ አስፈፃሚው አንስቶላቸው በመረጃ የተደገፈ የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ሠራተኞች ሲገኙ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ አሁን ላይ 4‚500 ሾፌር እና ገንዘብ ተቀባይ ሰራተኞች እንዳሉት እና በሥነ-ምግባር የታነጹ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ተከታታይነት ያለው ስልጠና እየሰጠ ሲሆን የአውቶብሶች የቀን ምልልስ ብዛት ከ6-7 የነበረው ከ12-14 ከፍ እንዲል ተደርጎ አሁን ላይ የተማሪ ባስን ጨምሮ 1,243 አውቶቡሶች በ192 መደበኛ መስመሮችን እና 14 የታክሲ ስምሪት ቦታዎችን መኖራቸውን ገልጸዋል።
በገቢ አሰባሰቡ ላይ በተደረገው ሪፎርም ምክንያት፣ ከዚህ ቀደም በቀን ከአራት ሚሊዮን ብር የማይበልጥ የነበረው ገቢ አሁን ላይ ወደ 12 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱንና “ትክክለኛ ባለሞያ ለትክክለኛ ሥራ” በሚል መርሕ በድርጅቱ ውስጥ እየሠሩ የሚገኙ 4,500 ሾፌሮች እና ገንዘብ ተቀባይ ሠራተኞች እንዳሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ አካሉ አሰፋ አስረድተዋል።
በያለው ጌታነህ