የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ መርሃ ግብር በህዝብና ተቋማት መካከል መተማመን በመፍጠር ለዲጂታል ሥርዓት ግንባታ ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።
የፕሮግራሙን ተቋማዊ አሰራርና ውጤታማነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ በአዋጅ 1284/2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
አዋጁ ነዋሪዎች የመታወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥ፣ ሌሎች መብቶቻቸውን የመጠቀም እድላቸውን ለማስፋት፤ በአገልግሎት ሰጭና ተቀባይ መካከል በሚኖር ግንኙነት እምነት እንዲዳብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና የተሳለጠ አሰራር ለመዘርጋት ያለመ ነው።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዲጂታል ኢትዮጵያን በማሳለጥ ማጭበርበርን ከማስቀረት በተጨማሪ በህዝብና በተቋማት መካከል መተማመንን ለመፍጠር ዲጂታል መታወቂያ ጉልህ ሚና አለው።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳና በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 2030 ውስጥ አንዱና ዋናው አስቻይ ምሰሶ መሆኑን ተናግረዋል።
ለተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት ለመስጠት አስቻይ ሁኔታን መፍጠር፤ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እና ለዲጂታል የህዝብ መሰረተ ልማት መሰረት በመጣል በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
እስካሁን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ያደረጉ ሰዎች ቁጥር 29 ሚሊየን መድረሱንም ጠቅሰዋል።
በፕሮግራሙ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች ባለ 12 አሃዝ ልዩ የፋይዳ መለያ ቁጥር እየተሰጠ እንደሚገኝና ይህ መለያ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ተደርገው እንደሚቆጠሩ አስረድተዋል።
በምዝገባ ሂደቱ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍን ጥሪ ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ ከተቋማት ጋር መተሳሰሩ የአገልግሎቱን ተጠቃሚ ቁጥር ለማሳደግ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።