ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል ያስመዘገቡት ድል በሁሉም ፈተናዎች እንደማይሸነፉና ፅናት እንዳላቸው ምርጥ ማሳያ መሆኑን መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የብሪክስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ ዳኛ የነበሩት አያንዳ ሆሎ ተናገሩ፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ ዳኛ የነበሩት የደቡብ አፍሪካዊ አያንዳ ሆሎ፤ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ለመዘገብ ወደ አዲስ አበባ ተመላልሰዋል፡፡
አያንዳ ሆሎ ወደ አዲስ አበባ በመጣሁ ጊዜ ከተማዋ ሁሌም አስደማሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን አይቻለሁ ብለዋል ::
በከተማዋ በሁሉም ቦታዎች የህንፃዎችና የተለያዩ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄዱና ከተማዋ በከፍተኛ ደረጃ እያደገች እንደምትገኝም መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች፤ በፈጠሪ ዘንድም የተባረከች ሀገር ናት ያሉት አያንዳ ሆሎ፤ ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ፋሺስት ጣሊያንን በማሸነፍ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት ድል በሁሉም ፈተናዎች እንደማይሸነፉና ፅናት እንዳላቸው ማሳያ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ድል ስኬት፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ የአፍሪካ ህብረት ምስረታ ለአፍሪካ ዘርፈ ብዙ አበርክቶ ያላት ሀገር በመሆኗ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፤ ይገባታልም ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የነፃነት እርሾ ምንጭ በሆነችው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ መካሄዱ ሌሎችንም የሚያነቃቃ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀደሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ስልጠና በመስጠት ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ አገዛዝ ስርዓት ነፃ እንድትሆን ታሪካዊ ድጋፍ ማድረግ መቻሏንም ጠቁመዋል፡፡