የአራዳ ክፍለ ከተማ 8ሺህ 2መቶ ዶሮዎችን የስራ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ላላቸው 5 መቶ 11 ለሚሆኑ ቤተሰቦች የእርባታ ዶሮዎችን ድጋፍ አደረገ ፡፡
ከክፍለ ከተማው ከ8ቱም ወረዳዎች ለተመለመሉ ነዋሪዎች የተሰጠው ይህ ድጋፍ ለሁለተኛ ዙር የተደረገ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር 4 መቶ 30 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መደረጉንም የአራዳ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደርቤ ተሾመ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።
ተጠቃሚዎች ከዚህ በፊት በራሳቸው ተነሳሽነት ዶሮዎችን እያረቡ የነበረ ሲሆን ይህንኑ መነሻ በማድረግ ስራቸውን እንዲያስፋፉና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ ክፍለ ከተማው በበጎ ፍቃድ ድጋፍ እንዳደረገላቸው በመርሃግብር ላይ ተነስቷል።
ድጋፉ በቤተሰብ ደረጃ የተደረገ ሲሆን ይህም የአንድ ቤተሰብ አባላት በአንድ ላይ በመደራጀት ሸማች ብቻ ሳይሆን አምራችም በመሆን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለገበያ ምርት በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በሔዋን አበራ