በአዲሰ አበባ ከተማ በመንገድ ዳር የሚቀመጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለዜጎች ጤና፣ ለከተማ ጽዳት እና ውበት የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል።
ኤ ኤም ኤን በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አከባቢ ባደረገው ቅኝት የመንገድ ዳር የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻለ ቢሆንም አሁንም ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ከማስወገድ አኳያ የሚቀሩ ተግባራት እንዳሉ ለመረዳት ችሏል።
ወ/ሮ ስንቄ ጥላሁን በከተማ ጽዳት ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ቅሻሻን ማስወገድ የመንገድ ላይ የጽዳት ሰራተኞች ሥራ ብቻ አድርጎ እንደሚቆጥር ይገልጻሉ፡፡
ዜጎች የተጠቀሙባቸውን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በአግባቡ እንዲያስወግዱ ግንዛቤ መፈጠር ሊፈጠር እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ቆሻሻን በአግባቡ በማያስወግዱ ሰዎች ላይ ቅጣት ሲጀመር አብዛኛው ሰው ቆሻሻን በአግባቡ በመለየት ማስወገደ ጀምሮ ነበር የሚሉት ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ ተሾመ ደበላ ከቅርብ ጊዚ ወዲህ ግን ሰዎች የተጠቀሙባቸውን ነገሮች በግድየለሽነት በየ ቦታው እና በቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች አጠገብ እንደሚጥሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ታደሰ መኮንን በበኩሉ ሰዎች የተጠቀሙበትን ነገር በችኮላ ቆሻሻ ማጠራቀሚያው ውስጥ መጣላቸውን እንጂ በአግባቡ እና እንደ ቆሻሻው አይነት ለይተው እንደማያስቀምጡ ይናገራሉ ።
በመዲናዋ በመንገድ ዳር ያሉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች የሚበሰብሱ እና የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን በመለየት እንደ አይነታቸው ለማስወገድ በሚያመች መንገድ የተዘጋጁ ቢሆኑም በአጠቃቀም ላይ ግን ክፍተት እንዳለ ለመረዳት ተችሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ ቆሻሻን ወደ ሀብት ለመቀየር የሚደገረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ፣ የራስ እና የአከባቢን ጤና ለመጠበቅ ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን ማሻሻል ይኖርበታል።
እርስዎስ ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ምን ታዝበዋል? ያጋሩን !
በፍሬሕይት ብርሃኑ