ሙስናን የመከላከል ትግል መላው ማህበረሰብ ፣ ሁሉም ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
ከንቲባ አዳነች በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ዛሬ 22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት እና የገባነውን ቃል በማደስ ነው” ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሙስናን የብልፅግና ፀር፣ የኢፍትሀዊነት ምንጭ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ ተደርጎ የተፋፋመው ትግል ከዚህ ቀደም የነበረውን አስከፊ መንግስታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ማስቻሉንም ከንቲባ አዳነች ጠቅሰዋል። በዚህም እንደ አገር ብሎም እንደ ከተማ የህዝብና የመንግስትን ሀብት በተገቢው የልማት ስራዎች ላይ በመዋሉ አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት ተችሏል።
መንግታዊ / ስርአታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ቢቻልም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚታይ በመንግስት ሃላፊዎች እና ሰራተኞ የሚፈፀመው ሌብነት እና ጉበኝነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋት እና ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር፣ መንግስታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆንና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል የሁሉንም ተቋማት ትግል እና የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል።
ቤተሰብ፣ ማህበረሰቡ፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችም አካላት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በፀረ ሙስና ትግል ውስጥ በአመለካከትም በተግባርም ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች ባሰፈሩት መልዕክት አፅኖት ሰጥተዋል።
የፀረ ሙስና ትግሉ ይበልጡን ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።