ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ኢግዚቢሽንና ባዛር ውድድር አሸናፊ ሆነ

You are currently viewing ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ኢግዚቢሽንና ባዛር ውድድር አሸናፊ ሆነ

AMN- ታህሳስ 3/2018 ዓ.ም

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ “12th Annual Winternational Embassy Showcase” በሚል ርዕስ በአሜሪካ የንግድ ማዕከል በተዘጋጀው ኢግዝቢሽንና ባዛር ላይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እምቅ አቅሞች በማስተዋወቅ መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ካደረጉ ከ70 ኤምባሲዎች መካከል አንደኛ በመውጣት የተዘጋጀውን ዋንጫ ተረክቧል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ቡናና ባህላዊ የአፈላል ስርዓት፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ትርኢት፣ ባህላዊ ምግብና መጠጦች፣ ባህላዊ የቡና አፈላል ስነ-ስርዓት የዝግጅቱ አካል የነበሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፕሮሞሽን፣ የተለያዩ የሀገራችን ባህላዊ ውዝዋዜዎች፣ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል ደግሞ የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ አል-ነጃሽ መስጂድ፣ ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ፣ የሰሜን እና ባሌ ተራሮችን ጨምሮ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብቶችን በፕሮግራሙ ላይ ቀርበዋል።

በፈረንጆቹ ህዳር 9 ቀን 2025 በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች በተሳተፉበት ውድድር፣ ዳኞች በሰጡት ምርጫ መሰረት፣ ኤምባሲው ከ70 ኤምባሲዎች መካከል ‘’The Best Embassy of the Year’’ በመባል የተዘጋጀውን ዋንጫ መረከብ ችሏል።

በኢግዝብሽንና ባዛር ላይ ከ8 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በመገኘት የኢትዮጵያን ቡና በመቅመስ በርካታ አሜሪካውያን፣ የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያን ኢንቬስትመንት ዕድሎች፣ ታሪካዊ ቅርሶችና የቱሪዝም መስህቦችን የሚያሳይ ቪዲዮ ለእይታ ቀርቧል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ እና ለመጎብኘት ከመጡት እንግዶች መካከል፣ የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህቦች ለመጎብኘት በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ የመጓዝ ፍላጎት እንዳላቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review