በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በሚገኝ አንድ የወፍጮ ቤት ውስጥ አብሮት የሚሰራ የሥራ አጋሩን ሕይወት በማጥፋትና ዘረፋ በመፈጸም የተሰወረ ተጠርጣሪ ከነግብረ-አበሩ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ መሠረት መስከረም 18 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ላይ ተጠርጣሪው ዘላለም ሀብታሙ ከግብረ-አበሩ ተመስገን ተስፋ ጋር በመመሳጠር፣ በወፍጮ ቤቱ የሚሠራ አጋሩ ዳንኤል ይልቃልን ሕይወት በማጥፋት 18 ኩንታል ጤፍ ዘርፈው ይሰወራሉ።
ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ክትትልና የቴክኒክ ምርመራ፤ ዋና ተጠርጣሪው ዘላለም ሀብታሙን በአዳማ ከተማ፣ ግብረ-አበሩን ደግሞ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወንጀሉ በተፈጸመ በ24 ሰዓታት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ሊያውላቸው ችሏል።
ተጠርጣሪዎቹ የዘረፉትን 18 ኩንታል ጤፍ በ171 ሺህ 200 ብር መሸጣቸውን ፖሊስ ደርሶበት፣ ንብረቱን በማስመለስ ለባለቤቱ ማስረክቡንም ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ፖሊስ፣ ኅብረተሰቡ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር መልዕክቱን አስተላልፏል።