“ስማርት የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎቹ ከተማችንን ስማርት ለማድረግ የጀመርነው ሥራ አካል ናቸው”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
‘የስማርት ከተማ አብዮት…’ በተሰኘው የማርክ ዴኪን እና ሁሳም አል ዋየር ጥናታዊ መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው 21ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም አቀፍ ከተሞች ፈጣን ለውጥ አምጥቷል። በብዙ መልኩ ተራርቀው የነበሩ ከተሞች የተቀራረቡ፣ ዘላቂነት ያላቸው እና በቴክኖሎጂ የሚመሩ ማዕከላት እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ወቅት በከተሞች መካከል ያለው የለውጥ አብዮት ከቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር አብሮ እየፈጠነ ስለመሆኑም በጥናታዊ መፅሐፉ ላይ ሰፍሯል፡፡
እንደ መፅሐፉ ከሆነ፣ የቴክኖሎጂ እድገት በከተማ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በዚህም ምክንያት የስሉጥ (ስማርት) ከተሞች ዕድገት በእጅጉ አየተፋጠነ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ እነዚህ ስማርት ከተሞች፣ ስልጡን የመጓጓዣ ዘዴዎች፣ ዘላቂ የኃይል መፍትሔዎች (የታዳሽ ኃይል አማራጮች)፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ያሏቸው ሲሆን፣ በኮሪደር ልማትም ሆነ በሌሎች ዘመኑን የዋጁ ስራዎች የተሻለ በመከወናቸው ለነዋሪዎቻቸውም ሆነ ለእንግዶቻቸው ምቹ ከተሞች መሆን ችለዋል፡፡
እንደ ሲንጋፖር፣ ባርሴሎና እና አምስተርዳም ያሉ ከተሞች የኮሪደር ልማትን በመሳሰሉ ዘርፎች በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ቀድመው በመጀመራቸው ሌሎች የዓለማችን ከተሞች የእነርሱን ፈለግ እንዲከተሉ መንገድ ስለመጥረጋቸውም በመፅሐፉ ተመላክቷል፡፡
አዲስ አበባ ከተማም ይህንን የሰለጠነ መንገድ በመከተል ላይ ስለመሆኗም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለአብነትም ባሳለፍነው ሐሙስ ታህሳስ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ሦስት ዘመናዊ ባለ 10 ወለል ስማርት የወረዳ አስተዳደር ሕንፃዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ የሕንፃዎቹን ወደ ስራ መግባት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ “ስማርት የአገልግሎት መስጫ አስተዳደር ሕንፃዎቹ ከተማችንን ስማርት (ስሉጥ) ለማድረግ የጀመርነው ሥራ አካል ናቸው” ብለዋል፡፡
ከተማን ማዘመን ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ እና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ሙህዲን ሙሐመድ እንደገለፁት በየትኛውም ሁኔታ፣ ከፍታና ዝቅታም ውስጥ ቢሆኑ ከተሞች ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ስኬታማነት ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ስማርት መሆን ከከተማዋ ሁለንተናዊ ከፍታ ባሻገር እንደ ሀገር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እምርታ የሚያመጣ ነው፡፡
በዚህ ዘመን ላይ ከተሞች የስልጣኔ፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ማዕከል ናቸው፡፡ በመሆኑም ከተማን ከስልጣኔ፣ ከዕድገት፣ ከልማት እና መሰል ዘመናዊ ነገሮች ልንለይ አንችልም ብለዋል፡፡

እንደ መምህር ሙህዲን ስለ ስማርት ሲቲዎች ስናነሳ ከዚህ ቀደም ባልሄድንበት መንገድ ነው የምንሄደው ብለን ማየት አለብን፡፡ ለአብነትም አዲስ አበባን ብንወስድ የኢትዮጵያ የስልጣኔ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ መስተጋብር፣ የፖለቲካ እና የተለያዩ ጉዳዮች ማዕከል ናት፡፡
እዚህ ላይ ስማርት ሲቲን ስናስብ ብዙ ዕድሎችን ይሰጠናል፡፡ ይህም ከተማዋ ስማርት ስትሆን ዜጎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው አፈፃፀም እንዲጨምር፣ ብክነት እንዳይኖር እና አገልግሎት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን፣ ቀልጣፋ ውሳኔ ለመስጠት፣ ዜጎችንም በተሻለ ሁኔታ ለማሳተፍና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያስችላል፡፡ ከተማዋ ስማርት ስትሆን ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፍ ለመጠቀም ትችላለች፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የአገልግሎት ተደራሽነት ይሰፋል፤ ቅልጥፍናውም ይጨምራልም ብለዋል መምህሩ በሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ በከተማዋ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት መካከል አንዱ ለህዝብ ቅርብ የሆኑ የወረዳ አገልግሎት መስጫዎችን ማዘመን፣ በበቂ የሰው ኃይል ማደራጀት፣ በቴክኖሎጂ መደገፍ እንዲሁም ለአገልግሎት ሰጭውና ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ምቹ የስራ ቦታን መፍጠር እንደሚገኙበትም ገልጸዋል፡፡
እንደ ከንቲባዋ ገለፃ ወደ አገልግሎት የገቡት ስማርት የወረዳ አስተዳደር ሕንፃዎች አገልግሎትን ወደ አንድ ማዕከል በመሰብሰብ ተገልጋዩ ጊዜና ሀብት እንዳይባክን በማድረግ፣ እንግልትና ውጣ ውረድን በመቀነስ፣ በአንድ ማዕከል ፈጣንና ቀልጣፋ የወረዳ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲያስችሉ ተደርገው የተገነቡ ናቸው፡፡
ሕንፃዎቹ ዘመናዊ መኪና ማቆሚያ፣ የልጆች ማቆያና መጫዎቻ ስፍራ፣ ውብ ፅዱና አረንጓዴ ቅጥር ግቢ እንዲኖራቸው ተደርገው ተገንብተዋል፡፡ በተጨማሪም አካል ጉዳተኞችን እና አቅመ ደካሞችን ታሳቢ ያደረገ አሳንሰር ወይም ሊፍት የተገጠመላቸው እንደሆነም ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞችም ስማርት ሲቲ መሆናቸው በቅርባችን ካሉ የሌሎች ሀገራት ከተሞች አንፃር የተሻለ ተወዳዳሪ እንድትሆን እና ከፍ ብላ እንድትወጣም ያደርጋታል ያሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር)፣ አዲስ አበባ በምስራቅ አፍሪካ፣ በቀጣናው እና እንደ አህጉር ያላትን ከፍታ ለማስቀጠል ስማርት መሆን ግድ ይላታል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ ለውጦች ይህንን የሚያመላክቱ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡

አርክቴክት እና የከተማ ፕላነር ሮበርት ሳሙኤል (ዶ/ር) ‘Timeless Cities’ ወይም ጊዜ የማሽራቸው ከተሞች የተሰኘ የምርምር መፅሐፍ አላቸው፡፡ በዚህ ስራቸው ከተሞች ሳያረጁ ከዘመን ጋር እየዘመኑ እና የህዝባቸውን አዳጊ ፍላጎት እያሟሉ ከፍ የሚሉበትን ምስጢሮች ተንትነዋል፡፡
ከተሞች አስደማሚ፣ ሰፊና ምቹ ጎዳናዎች፣ ደማቅ ሰፈሮች፣ በአረንጓዴ ዕፅዋት የታጀቡ እና ከግፊያውና ውክቢያው ገለል ብሎ ሰው ከራሱ፣ ከወዳጁ እና ከተፈጥሮ ጋር የነፍስያ ጨዋታ የሚኮመኩሙባቸው የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ትላንትን ከዛሬ አስማምተው የተሰሩ ልዩ ልዩ ግንባታዎች እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን በመተግበር ዜጎቻቸውን የሚያስደስት አሰራርን ተግባራዊ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ሮበርት (ዶ/ር) በጥናታዊ መፅሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም ከተሞች እንደዘመኑ ስልጡን፣ ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ፣ የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀንሱና ከተፈጥሮ ጋር የተዋደዱ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና የህዝብ ማመላለሻ አማራጮች የሚጠቀሙ፣ ያልተጨናነቁ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ የተለያዩ የኢኮኖሚ አማራጮችና ፈጠራዎች፣ አካታች ልማትና ማህበራዊ ፍትሕ የነገሰባቸው፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ ለነዋሪዎቻቸው ፍላጎትና ምቾት ቅድሚያ የሚሰጡ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ የሚያደርጉ መሆን እንዳለባቸውም ገልፀዋል፡፡
የለንደኑ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ጥናትና ምርምር ማዕከል ‘የስማርት ከተማና የምጣኔ ሀብት ተዛምዶ’ በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው የቅርብ ጊዜ ጥናት መሰረት ‘ስማርት ከተማ’ የሚለው ቃል የአንድን ከተማ የህዝብ አገልግሎቶች እና መሠረተ ልማቶችን ለማገናኘት እና ለማመቻቸት የታለሙ ስትራቴጂዎችን ስብስብ ያመለክታል። ስማርት ሲቲ የመጨረሻ አላማቸው የዜጎችን የኑሮ ጥራት ማሻሻል ነው። አንድን ከተማ ስማርት ናት ስንል በፈጠራ የተዋበች፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት የምትሰጥ፣ ዘላቂ እና እርስ በርስ የተገናኘች ናት ማለታችን ነው ይላል መረጃው፡፡
የስማርት ከተማ ልማት በ10 ዋና ዋና ምሶሶዎች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ እነዚህም የዘላቂ የከተማ ልማት መርሆዎችም ናቸው። እነሱም ስማርት አስተዳደር፣ ስማርት ኢኮኖሚ፣ ስማርት አካባቢ፣ ስማርት ማህበረሰብ፣ ስማርት ኑሮ፣ ስማርት የትራንስፖርትና መሰል እንቅስቃሴዎች፣ ስማርት አውቶማቲክ የመኪና ማቆሚያ ስርዓቶች፣ ዘመናዊ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች፣ ስማርት ኢነርጂ እና የአየር ብክለትን መቋቋም የሚችል ምቹ ስፍራ መኖር እንደሆነ በመረጃው ተመላክቷል፡፡
አዲስ አበባ ከተማም ከዘመኑ ጋር የተስማማሙ፣ የነዋሪውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነች ነው፡፡ በተለይም የስማርት ከተማ ልማት ምሶሶዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ነው፡፡ ባሳለፍነው ሐሙስ ታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም በልደታና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ተገንብተው ወደ አገልግሎት የገቡትን ሦስት ባለ 10 ወለል ህንፃዎችን ይህንኑ ያመላክታሉ፡፡ በቀሪዎቹ ወረዳዎችም ላይ የማስፋትና የማብዛት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መግለፃቸውም ይታወሳል፡፡
በመለሰ ተሰጋ